የንባብ ባህልን ያዳበረ ትውልድ እንዴት ይገነባል?

አዲስ አበባ ሚያዝያ 19/2015 (ኢዜአ)፦ የንባብ ባህልን ያዳበረ ትውልድ እንዴት ይገነባል?

"ኢትዮጵያ ታንብብ" በሚል መሪ ሃሳብ በወጣቶች ንባብ ባህል ዕድገት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ አብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ተካሂዷል።

በመድረኩም ከምሁራን ደራሲ ደረጀ ገብሬ፣ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ እና ዮናስ ዘውዴ የውይይት መነሻ ሀሳቦችን አቅርበው፤ ውይይት ተደርጓል።


 

የቋንቋ ምሁሩ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፤ 1960ዎቹ አብዮት በፊት የነበረው የተሻለ የንባብ ተሞክሮ በሂደት እያሽቆለቆለ "ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፈር፣ ማኅበረሰብ እና ሀገር አያነቡም" በሚያሰኝ ደረጃ ላይ ደርሰናል ሲሉ ተናግረዋል።

የንባብ ይዞታን ለማሻሻል ቤተ-መጽሐፍትን ብቻ ሳይሆን የሚታተሙ መጻህፍትን ተደራሽነት ማስፋት እና የናረው የመጻህፍት ዋጋ እንዲቀንስ መሰራት አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ የንባብ ባህልን ያዳበረ ትውልድ እንዴት ይገነባል? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ከምንም በላይ የህፃናት መጻህፍት ዝግጅትና ሥርጭት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል።


 

የንባብ ባህል እንዲዳብር መምህራን ኃላፊነታቸውን ሲወጡ፣ የመጻህፍት ሕትመት ሲበረታታና ሚዲያዎችም በንባብ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩ መሆኑን ያመላከቱት ደግሞ ደራሲ ደረጃ ገብሬ ናቸው።


 

ሌላው ሃሳብ አቅራቢ ዮናስ ዘውዴ ደግሞ፤ የማያነብ ሀገር እና ሕዝብ የመሻሻልና የመለወጥ ተስፋ የሌለው በመሆኑ ትውልድ የሃሳብ ጎተራ እንዲሆንና ሀገር ከመዳህ እንድትቃና የትውልዱ የንባብ ባህል መዳበር አለበት ብለዋል።

አንባቢና ያነበበውን ወደ ተግባር የሚለውጥ ትውልድ ለመገንባት ለአንባቢ ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም የዘመኑን ትውልድ ከዘመኑ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ጋር እንዴት አጣጥሞ መራመድ እንደሚቻል ሃሳብ ሰንዝረው ውይይት ተደርጓል።

ህፃናት ንባብ ማጎልበቻ ልማዶችን ማሳደግ ብሎም ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂዎችን ወጣቶች ከንባብ እንዲርቁ ሳይሆን ለንባብ እንዲጠቀሙባቸው ማድረግ ላይ መተኮር እንዳለበትም አንስተዋል።


 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ኢትዮጵያ በጽሑፍ ሀብት ብትታደልም የንባብ ባህልና የንባብ መንደር አለመኖሩ ያስቆጫል ብለዋል።

በመሆኑም ቤተ-መጽሐፍት በአስፈላጊነታቸው ልክ ሊገነቡና የሚጽፉና የሚያነቡ ዜጎችም ሊበረታቱ ይገባል ነው ያሉት።

የአሁኑ ትውልድም ምቹ ሁኔታ ከቀረበለት ማንበብ እንደሚችል የአብርሆት ተጠቃሚዎች ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የዩኒቨርሲቲና የመንግሥት ተቋማት ነባር የሕዝብ ቤተ-መጽሐፍት ማሻሻልና ተጨማሪ አብያተ- መጽሐፍትን በሁሉም አካባቢዎች ማስፋፋት ያስፈልጋል ብለዋል።

በመንግሥት በኩል የንባብ ባህል እንዲዳብር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር አብያተ-መጽሐፍት እና የመጻህፍት ተደራሽነት እንዲስፋፋና ከቴክኖሎጂ ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ የሕግና አሠራር ማዕቀፍ ማሻሻያዎች ለማድረግ እየተሰራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።


 

የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ዋና ዳይሬክተር ውባየሁ ማሞ፤ የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት በቀን በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞችን እያስተናገደ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌሎች መሰል ቤተ-መጽሐፍቶችን ማስፋፋት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም