በብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል የሴቶች ሊግ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የቦንድ ግዢ ንቅናቄ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል የሴቶች ሊግ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የቦንድ ግዢ ንቅናቄ ጀመረ
ሰመራ፣ ሚያዚያ 19/2015 (ኢዜአ) በብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል የሴቶች ሊግ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የቦንድ ግዢ ንቅናቄ በዛሬው ዕለት በሰመራ ከተማ አስጀመረ።
የፓርቲው የአፋር ክልል ሴቶች ሊግ ሃላፊ ወይዘሮ ኡርቲይያ የይስ በንቅናቄ ማስጀመሪያው ላይ እንደተናገሩት፤ ሴቶችን ጨምሮ የክልሉ ማህበረሰብ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።
አሁንም ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተው፤ የክልሉ ሴቶች ቦንድ በመግዛት የድርሻቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ዛሬ የተጀመረው የቦንድ ግዢ ንቅናቄ እስከ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ 10 ሚሊዮን 100 ሺህ ብር ለመሰብሰብ ግብ መቀመጡን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ዕቅዱን ለማሳካት በክልሉ ያሉ ሴቶችን በስፋት ለማሳተፍ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን እንዲሆን ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች ያላቸው ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት ጠቅሰው፤ በአገራዊ የልማት ፕሮጀክት ውስጥም ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ስለሆነም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ በማጠናከር አሻራቸውን ማሳረፍ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
በንቅናቄው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ቦንድ የገዙት ወይዘሮ ፋጡማ ሃንፈሬ በበኩላቸው የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ የዜጎችን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።
በመሆኑም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
ሌላኛዋ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ወይዘሮ ፋጡማ መሃመድ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል።
ሁላችንም ሴቶች በንቃት በመሣተፍ የቦንድ ግዢ እንዲፈፀም የራሳችንን ድርሻ እንወጣ ብለዋል።