ቀጥታ፡

ከ250 በላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች የተሳተፉበት የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ተከፈተ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 19/2015(ኢዜአ) ከ250 በላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች የተሳተፉበት የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፈተ።

የንግድ ትርዒቱ በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ አዘዘው፤ በመርሃ-ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር በማመቻቸት የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ሁነቱ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግሥትና በንግድ ምክር ቤቱ የገቢ ንግድን የመተካትና የወጪ ንግድን ለማጠናከር የጎላ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በሚካሄደው 13ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከ250 በላይ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች የተሳፉበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በንግድ ትርዒቱ የተሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በተለያዩ ጥሬ ዕቃዎችና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ የተሰማሩ መሆናቸው ታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም