በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወልቂጤ ከተማና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወልቂጤ ከተማና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል
አዲስ አበባ ሚያዚያ 19/2015(ኢዜአ):-በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርሐግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ ወልቂጤ ከተማና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት እኩል ተለያይተዋል።
በአዳማና ሳይንስ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አቤል ነጋሽና ጌታነህ ከበደ ከእረፍት በፊት ያስቆጠሯቸው ግቦች ወልቂጤ ከተማን መሪ ማድረግ ችለው ነበር።
ይሁንና ከእረፍት መልስ አብነት ደምሴና አብዱራህማን ሙባረክ ያስቆጠሯቸው ግቦች ኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አድርጎታል።
የወልቂጤ ከተማ አምበል ጌታነህ ከበደ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ 14 ከፍ አድርጓል።
ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ በ25 ነጥብ ከነበረበት 12ኛ ደረጃ ወደ 11ኛ ከፍ ብሏል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ11 ነጥብ ከነበረበት 16ኛ ደረጃ ወደ 15ኛ ከፍ ቢልም አሁንም ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በ21ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሐ-ግብር ወላይታ ድቻ ከመቻል ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።