በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም የፌዴራል ተቋማት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ተግባራዊ ይደረጋል- የግዥና ንብረት ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም የፌዴራል ተቋማት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ተግባራዊ ይደረጋል- የግዥና ንብረት ባለሥልጣን
ሚያዚያ 19/2015(ኢዜአ)፦ በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም የፌዴራል ተቋማት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ።
በጨረታ ሂደት 45 ቀን የሚፈጀውን አሠራር ወደ 15 ቀናት ዝቅ ለማድረግ የአዋጅ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።
በኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት አተገባበር ዙሪያ ባለሥልጣኑ ከተለያዩ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ ላይ በግዥ ሥርዓቱ ውጤታማ የሆኑ ተቋማት ተሞክሯቸውን ያቀረቡ ሲሆን አተገባበሩ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና የመፍትሔ ሀሳቦችም ቀርበዋል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሐጂ ኢብሳ፤ በ2014 ዓ.ም በተመረጡ ዘጠኝ ተቋማት ላይ የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰዋል።
ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ አተገባበሩ ወደ 74 የፌዴራል ተቋማት ማደጉን ጠቅሰው፤ በሚቀጥለው ዓመት በሁሉም የፌደራል ተቋማት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓቱ ይተገበራል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትን ተሞክሮ ያነሱት አቶ ሐጂ ባለፈው ዓመት 72 ሚሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙን ጠቅሰዋል።
በ2015 ዓ.ም. እስካሁን ባለው በተቀላጠፈ መንገድ 92 ሚሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙን አስታውሰው፤ የግዥ ሥርዓቱ በሁሉም የመንግሥት ተቋማት ቢተገበር አዋጭ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
በመሆኑም በቀጣዩ ዓመት በግዥ ሥርዓቱ እስከ 30 ሺህ አቅራቢዎች እንደሚካተቱ ጠቁመው፤ ለዘርፉ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በክልሎች ደረጃም በሲዳማ ክልል የግዥ ሥርዓቱ በሙከራ ደረጃ ይተገበራል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤
በዞኖች እና ወረዳዎችም በየደረጃው ተግባራዊ የሚሆኑበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የሕክምና ሜዲካል ኮሌጅ የግዥ ዳይሬክተር ተስፋዬ ደርቤ፤ ተቋማቸው የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረጉ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከፍተኛ የግዥ ባለሙያ አስቻለው ደጀኔ በበኩላቸው፤ የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓቱ በብዙ መልኩ አዋጭና ጠቃሚ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት የግዥ ሥርዓት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ለአቅራቢዎች፣ አስመጪዎችና የመንግሥት ተቋማት ሰፊ ግንዛቤ መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።