መንግስትና ብልፅግና ፓርቲ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን በማጠናከር የተሻለች ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰሩ ነው - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስትና ብልፅግና ፓርቲ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን በማጠናከር የተሻለች ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰሩ ነው - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 19/2015(ኢዜአ)፡-መንግስትና ብልፅግና ፓርቲ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን በማጠናከር የተሻለች ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ለልኡክ ቡድኑ ለተደረገው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ለረጅም ዘመናት መታገሉን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን መፃኢ እድላቸው እጅግ የተቆራኘ መሆኑን ተናግረዋል።
የትግራይ ህዝብን ጥቅምና ፍላጎት በተሟላ መልኩ የሚሳካው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በጋራ በመስራት ነው ብለዋል።
መንግስትም የብልፅግና ፓርቲም የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ህዝብ በፍጥነት መልሶ እንዲቋቋም በቁርጠኝነት ይሰራሉ ነው ያሉት።
በጦርነቱ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም በመተባበር በፍጥነት ማገገም እንደሚቻል ተናግረዋል።
የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከንቲባዎች ጉብኝትም ሰላምን የማፅናት አብሮነትን በተግባር የመግለጥ ጉዞ ነው ብለዋል።
የልዑካኑ ጉብኝት የኢትዮጵያ ህዝብ የተጎዱ አካባቢዎችን በጋራ ለመገንባት ያለውን ዝግጁነት የሚገልጽ ነው ብለዋል።
መንግሥት የጀመረውን ጥረት ይበልጥ በማጠናከር ሁሉንም አቅሞች አጠናክሮ ህዝቡን ከደረሰበት ጉዳት ለማውጣት በትጋት መስራቱን ይቀጥላል ብለዋል።
ለዚህም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያንና አጋር አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
መንግሥት ኢትዮጵያ ከግጭት አዙሪት ወጥታ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንባት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ልዑኩ ትግራይ ክልል በመገኘት በጦርነቱ የተከሰተውን ጉዳት ጎብኝቶ አጋርነቱን ስላረጋገጠ እናመሰግናለን ብለዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ ለሚሰራቸው ስራዎች የዛሬው ጉብኝት ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው የመልሶ ግንባታ ስራውን ለማፋጠንና ሰላምን አጠናክሮ ለመቀጠል በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው ዕሁድ "ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናፅና" በሚል መሪቃል በተካሄደው የሰላም የዕውቅና መርሐ ግብር ላይ የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለትግራይ ህዝብ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየትና የሰላም ጅማሮውን በተግባር ለማስቀጠል ወደ መቀሌ እንደሚሄዱ መግለጻቸው ይታወሳል።