የሸዋል ኢድ በአል የቱሪዝም ዘርፉንና የልማት እንቅስቃሴዎችን በማነቃቃት አስተዋጽኦ እያደረገ ነው-ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
የሸዋል ኢድ በአል የቱሪዝም ዘርፉንና የልማት እንቅስቃሴዎችን በማነቃቃት አስተዋጽኦ እያደረገ ነው-ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
ሐረር ሚያዚያ 19/2015 (ኢዜአ)፡- የሸዋል ኢድ በአል የቱሪዝም ዘርፉንና የልማት እንቅስቃሴዎችን በማነቃቃት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።
በሐረሪ ክልል የሸዋል ኢድ በዓል የመክፈቻ መርሃ-ግብር በክልሉ ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ ተከብሯል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በወቅቱ እንዳሉት የሸዋል ኢድ በዓል የሐረሪ ህዝብ ከሌሎች ወንድም እህቶቹ ጋር በመሆን በአብሮነት የሚያከብረው ነው።
በዓሉ አንድነትን፣ አብሮነትንና ወንድማማችነትን በሚያጎለብት መልኩ እየተከበረ መሆኑን አመልክተዋል።
በአሉ አብሮነትን በሚያጎለብት መልኩ እየተከበረ በመምጣቱ የቱሪዝም ዘርፉና የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲነቃቁ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የክልሉን መልካም ገጽታ ለመገንባት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።
"የሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንና የማንነታችን መገለጫ የሆኑ አኩሪ ባህሎቻችንንና እሴቶቻችንን ጠብቆና ተንከባክቦ ማስቀጠል ከሁላችንም ይጠበቃል" ሲሉ አስገንዝበዋል።
ዘንድሮ በዓሉ "ሸዋል ኢድ ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለአብሮነትና ለቱሪዝም እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር ጠቁመው መሪ ሀሳቡን በተጨባጭ ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባ አመልክተዋል።
የአብሮነትና አንድነት መገለጫ የሆነውን የሸዋል ኢድ አከባበር በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርት እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸው አኩሪ ባህል፣ ታሪክና የጋራ እሴት ያላቸው መሆናውን ገልፀዋል፡፡
ሀረሪ አኩሪ ታሪክና ቅርስ የሆነውን በዩኔስኮ በማስመዝገብ ኢትዮጵያን ከፍ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው ክልሉ አሁን ላይም የሸዋል ኢድ በአልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በአሉ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በክልሉ የሚገኙ አንድ የግልና ሶስት የመንግስት ሙዚየሞች ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አገር አቀፍ እውቅና ተበርክቶላቸዋል፡፡
እውቅና ካገኙት መካከል በክብር ዶክተር አብደላ አሊ ሸሪፍ የተቋቋመ የግል ሙዚየም አንዱ ሲሆን ግለሰቡም በቅርስ ጥበቃ የጀጎል አዋርድ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
የክብር ዶክተር አብደላ ሸሪፍ የተበረከተላቸው እውቅናና ሽልማት በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዘርፍ የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆናቸው ገልጸዋል፡፡
በሙዚየማቸው የያዙት ታሪክ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ታሪክ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ካሁን ቀደም ያደረጉላቸውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
በበአሉ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችን ጨምሮ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የባህል ቡድኖች እና እንግዶች ተሳትፈዋል።