የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር "ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ " በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር "ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ " በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አበረከተ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 19/2015(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር " ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ " በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አበረከተ፡፡
የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ተወካይ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ መጽሃፍቱን ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አስረክበዋል፡፡
የታሪክ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ የማህበሩ መቋቋም ዋና ዓላማ ማህበረሰቡ ትክክለኛ የታሪክ አረዳድን እንዲያውቅና ታሪክ የመፍትሄ አካል እንዲሆን ለማስቻል ነው ብለዋል፡፡
በሌላ መልኩ ታሪክ ለአገራዊ መግባባት ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚችል ማስረዳትም የማህበሩ ዓላማ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዛሬው ዕለት ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተበረከተው ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ የተሰኘው መጽሐፍ የ18 የጥናት ጽሁፎችን ሃሳብ መያዙን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊ ኮሚሽን በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ስራዎች ከታሪክ አንጻር ያሉ እውነታዎችን ለመረዳት የተበረከተው መፅሃፍ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ከማህበሩ የተረከቡት መጽሃፍ ለኮሚሽኑ ስራዎች አጋዥ መሆኑን ጠቅሰው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በበኩላቸው የመጽሐፉ አበርክቶት ወቅታዊ እና ገንቢ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።