የከንቲባዎች ፎረም የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የከንቲባዎች ፎረም የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ሚያዝያ 19 / 2015(ኢዜአ)፦ ለከተሞች ልማትና ለዘመናዊ አሰራር ስርዓት መዳበር የልምድ ልውውጦች የሚደረጉበት የከንቲባዎች ፎረም በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።
የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሰኒ፤ ፎረሙን በማስመልከት ለመገናኛ በዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ከ300 በላይ የተለያዩ ከተሞች ከንቲባዎች የሚሳተፉበት ፎረም የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችና ከንቲባዎች በልማትና የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ይወያያሉም ብለዋል።
የከንቲባዎቹ ፎረም ዋነኛ ዓላማም ለከተሞች ልማትና ለዘመናዊ አሰራር ስርዓት መዳበር የልምድ ልውውጦች የሚደረጉበት መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች አብሮ ለማደግ እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ፎረሙ የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የገጠማቸውን ከተሞች መልሶ ለመገንባትም እንዲሁ።
ፎረሙ በከተማና መሰረት ልማት ሚኒስቴር እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ ትብብር የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል።