በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከቡና፣ የሻይና የቅመማቅመም ምርቶች ከ907 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከቡና፣ የሻይና የቅመማቅመም ምርቶች ከ907 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 19/2015(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቡና፣ የሻይና የቅመማቅመም ምርቶች ከ907 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፤ በቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ምርቶች የበጀት ዓመቱን ዘጠኝ ወራት የወጪ ንግድ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በባለሥልጣኑ የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ ካሳሁን ገለታ፤ የውጭና የውስጥ ተግዳሮቶችን በመቋቋም የነበረው ክንውንና የተገኘው ውጤት ጥሩ የሚባል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ169 ሺህ ቶን በላይ የቡና፣ ሻይና የቅመም ምርቶች ለውጭ ገበያ መቅረባቸውን ገልጸዋል።
የምርቶቹ መዳረሻ የነበሩት ሀገራትም ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ አሜሪካ፣ ኬንያ፣ እንግሊዝ፣ ቻይና፣ ሕንድ እና ሌሎችንም እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 907 ነጥብ 56 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል።
ከዕቅዱ አንፃር ለውጭ ገበያ የቀረበው ምርትና የተገኘው ገቢ ቅናሽ ቢያሳይም በዓለምና በአገር ውስጥ ከነበሩ በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች አንፃር የተገኘው ውጤት ጥሩ የሚባል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ምርቶችን በጥራትና ብዛት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በ2014 በጀት ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።