ኮሪያ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ በዓለም የስራ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት የጀመረችውን የማሻሻያ ስራ እንደምትደገፍ ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ኮሪያ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ በዓለም የስራ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት የጀመረችውን የማሻሻያ ስራ እንደምትደገፍ ገለጸች
አዲስ አበባ ሚያዚያ 19/2015 (ኢዜአ):- ኮሪያ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ በዓለም የስራ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት የጀመረችውን የማሻሻያ ስራ እንደምትደገፍ አስታወቀች።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ካንግ ሶኪ ጋር የትብብር ማዕቀፎችን ለማጠናከር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።
የወጣቱን የፈጠራ ችሎታ ለማውጣትና ለማዳበር የሚያስችሉ ሳይንሳዊ ዘዴዎችን ከኮሪያ ሪፐብሊክ እድገት ልምድ በመውሰድ በትብብር ለመስራት ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።
አምባሳደር ካንግ መንግስታቸው ወደ ኮሪያ ሪፐብሊክ የሰለጠነ የሰው ኃይል መላክን ጨምሮ የትብብር መስኮችን በማስፋት በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል።
ኮሪያ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ በዓለም የስራ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት የጀመረችውን የማሻሻያ ስራ እንደምትደገፍ አምባሳደሩ መግለጻቸውን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።
አምባሳደሩ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለኮሪያ ሪፐብሊክ የስራ ገበያ በማቅረብ ረገድም ኢትዮጵያ ዋነኛ ተመራጭ መዳረሻቸው መሆኗና “በአፍሪካ የመጀመሪያ ጥያቄው የቀረበላት ሀገር” መሆኗንም ገልጸዋል::
ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች ከኮሪያ ሪፐብሊክ ሕዝብ ጎን በመቆም ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሁልጊዜም በባለውለታነት ለሚታወሰው ተግባር በሕዝብና መንግስታቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል::
ወይዘሮ ሙፈሪያት አምባሳደር ካንግ ሶኪና የስራ ባልደረቦቻቸው በአዳዲስ የትብብር ማዕቀፎች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ላሳዩት ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት አመስግነዋል።