ቀጥታ፡

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 19/2015(ኢዜአ)፦ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወልቂጤ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይጫወታሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ10 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ በ24 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ሶስት ጊዜ ተሸንፏል ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

ሶስት ጊዜ ተሸንፏል፤ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ21ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ወላይታ ድቻ ከመቻል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ወላይታ ድቻ በ24 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን መቻል በ26 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

ወላይታ ድቻ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አላሸነፈም።

ሁለት ጊዜ ተሸንፏል፤ሶስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ደግሞ ሽንፈት አስተናግዷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻ 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ21ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባ ምንጭ ከተማን እንዲሁም ፋሲል ከነማ ሃዋሳ ከተማን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም