በብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የተመራ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ልዑካን ቡድን ወደ መቀሌ አቀና - ኢዜአ አማርኛ
በብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የተመራ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ልዑካን ቡድን ወደ መቀሌ አቀና
አዲስ አበባ ሚያዝያ 19/2015(ኢዜአ):- በብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የተመራ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች የልዑካን ቡድን ዛሬ ወደ መቀሌ አቅንቷል።
የልኡካን ቡድኑ የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች እና የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችን ያካተተ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው ዕሁድ "ጦርነት ይብቃ-ሰላምን እናፅና" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የሰላም የዕውቅና መርሐ-ግብር ላይ የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለትግራይ ህዝብ አጋርነታቸውን ለማሳየት ወደ መቀሌ እንደሚሄዱ ገልጸው ነበር።
የጉዞው ዓላማም "ያነቡ ዓይኖችን ለማበስ የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ክልሎች እንደወንድም ህዝብ ካላቸው ለማጋራት እና የሰላም ጅማሮውን በተግባር ለማስቀጠል ነው" ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ሁሉም ህዝብ ከትግራይ ወንድም ህዝብ ጎን መሆኑን የሚያሳዩበት ትልቅ ሁነት መሆኑንም ጠቁመዋል።
መንግሥት እና ህወሓት ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት ለማቆም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎም መንግሥት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ማቋቋምና እና የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ግንባታ እያካሄደ ነው።
በተለይ በትግራይ ክልል የባንክ የቴሌኮም የውሃ የመብራትና መሠል መሠረታዊ አገልግሎቶችንም አስጀምሯል።
የሰላም ስምምነቱን በተግባር በማስቀጠል ዘላቂ ሰላምን በኢትዮጵያ ለማስፈንም እየተሠራ ነው።
ኢትዮጵያ የጦርነትን ምእራፍ በመዝጋት ታሪካዊውን የሰላም ስምምነት "ጦርነት ይብቃ - ሰላምን እናጽና" በሚል መሪ ቃል ሚያዚያ 15/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ በድምቀት አክብራለች።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አብቅቶ ሁሉም ወገኖች የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ሚና ለነበራቸው አካላትም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።