ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው አካታች ልማትና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለግሉ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ሰጥታለች-ሚኒስትር አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 18/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው አካታች ልማትና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን ለመገንባት ለግሉ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ማስተዋወቅን ያለመ "ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023" ፎረም በአዲስ አበባ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።


 

ለሦስት ቀናት በሚቆየው ፎረም ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፤ ኢትዮጵያ ጠንካራ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት ሁሉን አቀፍ ሪፎርም እያካሄደች መሆኑን አብራርተዋል።

መንግስት ቀጣይነት ያለውና አካታች ልማት እንዲሁም የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሀገር በቀል ምጣኔ ሃብት ማሻሻያ መርሃ ግብርን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በዚህም በግሉ ዘርፍ የሚመራ አካታች፣ ተወዳዳሪና ቀጣይነት ያለው ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።


 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ በበኩላቸው ፎረሙ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለኢንቨስተሮች ለማስተዋወቅ ትልቅ አጋጣሚ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር ዋና ዋና የሚባሉ ዘርፎችን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ማድረግን ጨምሮ ሌሎች ሪፎርሞችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በግብርና፣ በማዕድን፣ በቤት ልማት፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በታዳሽ ኃይልና በሌሎች ዘርፎች ዕምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውን በመጠቆም ባለሃብቶች በየዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ አመቺ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ፣ አምራች የሰው ኃይል፣ የሎጅስቲክስ አቅርቦትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።


 

ኮሚሽነር ለሊሴ አክለውም መንግስት በኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋያቸውን ፈሰስ ለሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው የኢንቨስትመንት ፎረም ባለሀብቶችን፣ የፋይናንስ ተቋማትን፣ መሰረተ ልማት አቅራቢዎችን፣ የልማት አጋሮችንና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮችን ያገናኘ መድረክ ነው።

በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያሳይ አውደ ርዕይም ለፎረሙ ታዳሚዎች ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም