ቀጥታ፡

የውጭ ባለሀብቶች በቱሪዝም፣ በጤና፣ በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ያሉ ዕምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 18/2015 (ኢዜአ) ፡-የውጭ ባለሀብቶች በቱሪዝም፣ በጤና፣ በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ያሉ ዕምቅ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀረበ። 

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 'ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023' ፎረም ላይ በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ለተሳታፊዎች ቀርበዋል። 

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ባቀረቡት ገለፃ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመራጭ ከሆኑ የቱሪስት መዳረሻ ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም በቱሪስት አገልግሎት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል አለመጣጣም አለ ብለዋል።

በሌላ በኩል የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ገበያ እያደገ መምጣቱ፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ማዕከል በመሆኗ ዘርፉ በፍጥነት እያደገ ስለመምጣቱ አንስተዋል።

በጎብኝዎች መዳረሻ ልማት፣ በሆቴል፣ ምግብ አገልግሎት፣ በጉዞ እና አስጎብኚ ድርጅት፣ በኪነ ጥበብና መዝናኛ ስፍራዎች፣ የማይስ ቱሪዝም፣ በቱሪስት ማጓጓዣ፣ የኦንላይን የጉዞ መረጃዎች አቅርቦት፣ በውሃና አየር ትራንስፖርት ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዳሉ አስረድተዋል።

ቱሪዝም ትኩረት ከተሰጣቸው ቁልፍ የትኩረት ዘርፎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ጨምሮ ምቹ እና ሳቢ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች በመኖራቸው ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው በጤናው ዘርፍ የግል ባለሃብቶች ተሳትፎ እንዲያድግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የበሽታ መከላከልና ህክምና ስራ ሰፊ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ መሆኑ እንዲሁም የህዝቡ የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ፍላጎት እያደገ መምጣቱ ባለሀብቶች በዘርፉ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው አንስተዋል።

በመንግስት በኩል ያለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ የጤና ባለሙያዎችን የሚያፈሩ የጤና ትምህርት ተቋማትና ፕሮግራሞች ማደግ፣ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት መጀመር ኢትዮጵያን በጤናው መስክ ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለልብ፣ ለአዕምሮ፣ ለዐይን ህክምና እና መሰል የሪፈራል ህክምና ወደ ውጭ እንደሚሄዱ ገልፀው፣ ባለሀብቶች በህክምናው መስክ በመሰማራት የህክምና ማዕከላትን፣ የመድሃኒት ፋብሪካዎችን እና ላብራቶሪዎችን ቢያቋቁሙ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት። 

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ በዘርፉ የተሻሻሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።


 

የመንግስት ቁርጠኝነት፣ የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የተማረ እና ሰፊ የህዝብ ቁጥር መኖሩ ባለሀብቶች በትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዘርፍ ሙዓለ ንዋያቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በመንግስትና በግል ቅንጅት ከወደብ ወደ ወደብ ልማት፣ የባቡር ልማት፣ የሎጅስቲክስ ከተማ ልማት እንዲሁም በአቪየሽን ዘርፎች በርካታ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን መታቀዱን ገልፀዋል። 

በዚህም የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ መስክ ያለውን ዕምቅ የኢንቨስትመንት ዕድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም