የፈጠራ ሥራዎችን ለማጠናከር የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የፈጠራ ሥራዎችን ለማጠናከር የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ገለፀ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 18/2015 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ያሉ የፈጠራ ሥራዎችን ለማጠናከር የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ገለፀ።
የዓለም አእምሯዊ ንብረት ቀን "ሴቶችና አዕምሯዊ ንብረት፣ ኢኖቬሽንና ፈጠራን ማፋጠን" በሚል መሪ ሀሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ20ኛ ጊዜ በዛሬው ዕለት ተከብሯል።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለ ሞሲሳ የዘንድሮው የአዕምሯዊ ንብረት ቀን ሴቶች ላይ ያተኮረበት ምክንያት ሴቶች ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን ሰርተው እንዲያስመዘግቡ ለማበረታታት ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ ያሉ የፈጠራ ሥራዎችን ለማጠናከር የሴቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ ከተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር እንዲገናኙ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂና ፈጠራ ያደጉ ሀገራት ውስጥ ያለው የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ በመሆኑ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይህንኑ ለማሻሻል ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው፤ በሁሉም ዘርፎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ብዙ ስራ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በተለይም ሴቶች በፈጠራ ሥራዎች ላይ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ሁሉም ማበረታታት እንደሚገባው እንስተዋል።
የአዕምሯዊ ንብረት ቀን ሴቶችን ታሳቢ ያደረገውም ሴቶች የአዕምሯዊ ንብረታቸውን እንዲጠቀሙና ተሳታፊነታቸው እንዲጨምር ማድረግ ነው ብለዋል።