የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ በበጎ መልኩ የሚታይ ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ በበጎ መልኩ የሚታይ ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሚያዚያ 18/2015(ኢዜአ):- የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ በበጎ መልኩ እንደሚያየው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ትብብር በአዲስ መልክ እንደገና ለማደስ አበክራ እየሰራች እንደምትገኝም ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት ካደረገው ስብስባ በኋላ ከትናንት በስቲያ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ዙሪያ የፕሬስ መግለጫ አውጥቷል።
ሚኒስቴሩ ምክር ቤቱ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ ላይ የተገኙ ውጤቶችን ጨምሮ ለሌሎች ጉዳዮች እውቅና መስጠቱን ገልጿል።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ትብብር በአዲስ መልክ እንደገና ለማደስ አበክራ እየሰራች እንደምትገኝና የምክር ቤቱ መግለጫም ይሄንኑ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን አመልክቷል።
ሕብረቱ በዘላቂ ግብርናና የምግብ ዋስትና ላይ ያተኮረውን ዓመታዊ የባለብዙ ዘርፍ የድጋፍ ፕሮግራም በድጋሚ ለመጀመር ያሳየውን ዝግጁነት፣ አበዳሪ አገራት ባቋቋሙት የጋራ ማዕቀፍ ስር የሚከናወነው የኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ የድርድር ሂደት በአፋጣኝ እንዲቋጭ ያቀረበው ጥሪና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማረጋጊያና ማሻሻያ አጀንዳ እንዲደግፉ የሰጠው ጠንካራ ማበረታቻ መልካም የሚባል እንደሆነ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረትና ሌሎች ወዳጆቿ ጋር ያላትን ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የማስቀመጫው ጊዜ አሁን ነው ብሏል ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ።
የኢትዮጵያ አጋሮች ከአገሪቷ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በአዲስ መልክ እያደሱ ይገኛል ያለው ሚኒስቴሩ ይህ እየሆነ ያለው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ለማጽናት የተጀመረው ሂደት አስደማሚ ለውጦች በተመዘገቡበት፣የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች፣በግጭት የተጎዱ ማህበረሰቦችን መልሶ ማቋቋምና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ውጤቶች እየተገኙ ባሉበት ወቅት መሆኑን ገልጿል።