ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰራተኞች ማህበር በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 18/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰራተኞች ማህበር በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች አጋጥሞ በነበረው ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

የገንዘብ ድጋፉን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰራተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ኦላኒ ሴቃታ ለኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም አስረክበዋል።  

አቶ ኦላኒ ሴቃታ በዚሁ ወቅት፣ ማህበሩ በተለያዩ ጊዜያት በሀገሪቱ ባጋጠሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮዊ  ችግሮች ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።

በዛሬው እለትም የተደረገው ድጋፍ፣ በኦሮሚያ ክልል ቦረና፣ በደቡብና በሶማሌ ክልሎች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰራተኞች ማህበር ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

በቀጣይም እንዲህ ያሉ መሰል ተግባራት በሁሉም ተቋማት ሊበረታቱ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ያጋጠሙትን የድርቅ እንዲሁም የተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በዚህም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም