ቀጥታ፡

የትግራይ ክልል ወደ አገር አቀፍ የስፖርት ውድድር መድረክ ሊመለስ ነው

አዲስ አበባ ሚያዚያ 18/2015(ኢዜአ)፦ የትግራይ ክልል ከሁለት ዓመት በኋላ በአገር አቀፍ የስፖርት ውድድር መድረክ ሊመለስ  መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።

የስፖርት ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ተክላይ ፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ክልሉ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከሁለት ዓመት በላይ በአገር አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ሳይሳተፍ ቆይቷል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የክልሉን የስፖርት ልማትና እንቅስቃሴ ወደነበረበት ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ መልሶ የማቋቋምና የማደራጀት ተግባራት መጀመሩን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች ጋር ፍሬያማ ውይይቶች መካሄዳቸውንና የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ መደረጉን ኮሚሽነሩ በማሳየነት ጠቅሰዋል።

ከፌዴሬሽኑ ጋር በተደረጉ ውይይቶች የትግራይ ክልል በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም በሚካሄደው 52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንዲሳተፍ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንና ክልሉ በሻምፒዮናው ላይ እንደሚሳተፍ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሃብት አሰባሰብና ኮሙኒኬሽን የስራ ሂደት ኃላፊ ስለሺ ብስራት በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ ከሳምንት በፊት ከትግራይ ክልል ስፖርት ቢሮና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች ጋር መወያየቱን አስታውሰዋል።


 

የክልሉን አትሌቲክስ ስፖርት መልሶ የማደራጀት እንዲሁም የአትሌቲክስ ማዕከላትና ፕሮጀክቶችን የማቋቋም ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁሉንም ክልሎች ባሳተፈ መልኩ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከግንቦት 8 እስከ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እንደሚካሄድም ነው ኃላፊው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም