ቀጥታ፡

የውጭ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በመስኖ ልማት ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 18/2015(ኢዜአ)፡-የውጭ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በመስኖ ልማት ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ጥሪ አቀረቡ። 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለውጭ ባለኃብቶች የሚያስተዋውቅ መድረክ አዘጋጅቷል። 


 

በመድረኩ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የውጭ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በመስኖ ልማት ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል። 

በኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘመናዊ የመስኖ ልማት ሥራዎችን ለማስፋት ትኩረት ተደርጓል ብለዋል። 

በተለይም  አገሪቱ ያላትን የመልማት አቅም እንዲሁም የአየር  ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ከግምት በማስገባት ለመስኖ ልማት ትኩረት መሠጠቱን ተናግረዋል። 

ይህንንም ተከትሎ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የመስኖ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ በፖሊሲ የተደገፉ በርካታ ተግባራት እያከናወነ ነው ብለዋል። 

ያም ሆኖ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ10 እስከ 20 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ የመልማት አቅም ያለው ሲሆን እስካሁን በመስኖ የለማው መሬት ከ10 በመቶ በታች መሆኑን ጠቁመዋል። 

በመሆኑም በተለይም በትናንሽ የእርሻ መሬቶች ላይ የሚካሄደው የመስኖ ልማት ሥራ በመቀየርና በትላልቅ መሬቶች ላይ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል። 

ከዚህ ጎን ለጎን  የውጭ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በመስኖ ልማት ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፉ ነው የጠየቁት። 

በተለይም በመስኖ ልማት ዘርፍ ያሉትን የመስኖ መሠረተ ልማቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ የሚያውሉ ኢንቨስትመንቶች ይዘው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል። 

በተጨማሪ የውጭ ባለኃብቶቹ  ከአካባቢ ጋር የሚስማማና ዘላቂነት ያለው ቴክኖሎጂ  ገቢራዊ የሚያደርግ የመስኖ ልማት ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሠማሩ ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም