ቀጥታ፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ20ኛ መደበኛ ስብሰባው በመካከለኛ ዘመን (2016 - 2020) የማክሮ ኢኮኖሚና ፊሲካል ማዕቀፍ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

 

አዲስ አበባ ሚያዝያ 18/2015(ኢዜአ)፦የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባው በመካከለኛ ዘመን (2016 - 2020) የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊሲካል ማዕቀፍ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባው የተወያየው በመካከለኛ ዘመን /2016-2020/ የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊሲካል ማዕቀፍ ላይ ሲሆን ማዕቀፉ በዋናነት የመንግስት በጀት ከማክሮ ኢኮኖሚ ዓላማዎችና ታሳቢዎች ጋር ተጣጥሞ የተዘጋጀ መሆኑን፣ የመካከለኛ ዘመን የመንግስት ገቢና ወጪ እንዲሁም የፊሲካል ሚዛን የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለመለየትና ለማመላከት የሚያገለግል የበጀት ዕቅድ መሳሪያ ሆኖ የ2016 የፌዴራል መንግስት ዝርዝር በጀት የሚዘጋጅበትን ጥቅል የገቢ ትንበያ፣ የወጪ ጣሪያ፣ የክልላዊ መንግስታት የበጀት ድጋፍ ጣሪያ እና የፊሲካል ጉድለት መጠንን የሚያመላክት ሆኖ መዘጋጀቱን ምክር ቤቱ አረጋግጧል፡፡

በመሆኑም ማዕቀፉ ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት የተጋረጠውን የፊሲካል ስጋት ለመቅረፍ እና የፊሲካል ጤናማነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የፋይናንስ አጠቃቀም ስልት ተግባራዊ እንዲደረግ የሚያስችል መሆኑን በማመን፣ የመንግስት ገቢና ወጪ እንዲመጣጠን ማድረግን ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ግምት ውስጥ በማስገባት ምክር ቤቱ በማዕቀፉ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም