ቀጥታ፡

የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ይከናወናል

አዲስ አበባ ሚያዚያ 18/2015(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) ከ23 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድርን እንደምታስናግድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ውድድሩ በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልጿል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የሴካፋ የስራ ኃላፊዎች ትናንት በበይነ መረብ ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ውድድሩን እንድታስተናግድ ከመግባባት ላይ መደረሱን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

ውድድሩ የሚካሄድበት ስታዲየም በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቋል።

የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ውድድር ሴካፋ እ.አ.አ በ2023 ከሚያካሂዳቸው የተለያዩ ውድድሮች መካከል አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ ይህን ውድድር በ2013 ዓ.ም በባህር ዳር ስታዲየም ላይ ማዘጋጀቷን ፌዴሬሽኑ አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም