በወጣቶች ስነ-ምግባርና ስብዕና ግንባታ ስራ ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን ሊያጎለብቱ ይገባል-- ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በወጣቶች ስነ-ምግባርና ስብዕና ግንባታ ስራ ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን ሊያጎለብቱ ይገባል-- ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዳማ ሚያዝያ 18/2015 (ኢዜአ)፡- በወጣቶች ስነ-ምግባርና ስብዕና ግንባታ ስራ ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመቻችነት 'የወጣቶች ዘርፍ የሚዲያ ፎረም' ለመመስረት የተዘጋጀ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ እንደገለፁት ኢትዮጵያ ትልቅ የወጣቶች ቁጥር ያለባት አገር ናት።
ይህም በመሆኑ በወጣቱ የስብዕናና ስነ-ምግባር ዙሪያ ብዙ መስራት ስለሚያስፈልግ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
እስካሁንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራና በስብዕና ግንባታ ላይ መገናኛ ብዙሃንን ለማሳተፍ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።
በቀጣይም በመላ አገሪቷ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
የወጣቶች ሞራልና ስነ-ምግባርን የሚጎዱ ልምምዶችን መከላከልና ወጣቶች ተገቢው ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማስቻል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሐመድ ኢንዲሪስ በበኩላቸው የወጣቶችን ስነ-ምግባርና ስብዕና ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
በተለይ ወጣቶችን የሚጎዱ ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ መገናኛ ብዙሃን የድርሻቸውን ማበርከት አለባቸውም ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ከፌዴራልና ክልሎች የተወጣጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።