ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 18/2015(ኢዜአ)፦በአፍሪካ አራት አገራት ጉብኝት እያካሄዱ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ትናንት ወደ ቡጅምቡራ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ኤቨርስቴ ንዳይሽሚዬ ጋር በሁለትዮሽ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ መንግሥት በአሁኑ ወቅት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የማፅናት እና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ቁርጠኝነት ወስዶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የናይል ተፋሰስ አባል አገራት መደበኛው የምክክር ሂደት እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ምንጊዜም ከሱዳን ህዝብ ጎን እንደምትቆም ገልፀዋል።

የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ኤቨርስቴ ንዳይሽሚዬ በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ዳግም አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት ለአፍሪካ ሰላም ወሳኝ ሚና ይጫወታል ያሉት ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ የሰላም ሂደት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ቡሩንዲ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚፈጠሩ ልዩነቶች ሦስቱ አገራት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ውስጥ በውይይት መፍታቱን እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።

በናይል ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የሚነሱ ልዩነቶችን ሁሉም የተፋሰሱ አባል አገራት በውይይት መፍታት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ሌሎች አባል አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት በማያስከትል መልኩ ወንዙን ለልማት የመጠቀም እና የበርካታ ዜጎቿን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ የመለወጥ መብት አላት ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከቡሩንዲ ጉብኝታቸው አስቀድሞ በታንዛንያና ኮሞሮስ ባደረጓቸው ጉብኝቶች ከአገራቱ መሪዎች ጋር የሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ በትብብር መስራት የሚያስችሉ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም