የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑ ተገለጸ
ጅግጅጋ ሚያዝያ 18/2015(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት በመፍጠር ስራ አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ጭምር ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረግ የተቻለበት ውጤት መገኘቱ ተገለጸ።
የኢንዱሰትሪ ሚኒስቴር፣ የክልል እና ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮዎች እና ተጠሪ ተቋማት የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርት ግምገማ እና የምክክር መድረክ በጅግጅጋ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ መድረክ ላይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንዲሁም የፌዴራል፣ የክልል፣ የከተማ አስተዳደርና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በዚህም በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት በኢንዱስትሪው ዘርፍ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተከናወኑ የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርቶች ቀርበው የምክክር ግምገማ ይደረግባቸዋል ተብሎም ይጠበቃል።
በመድረኩም "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት በመፍጠር ስራ አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ጭምር ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረግ የተቻለበት ውጤት መገኘቱ ተገልጿል።
በዚሁ ወቅት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ፣ ኢንዱስትሪ ለአንድ አገር እድገት ወሳኝ ከሆኑ ዘርፎች ግንባር ቀደሙ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአገር እድገት የሚለካው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በሚደረግ ቀጣይነት ያለው መዋቅራዊ ሽግግር መሆኑንም ተናግረዋል።
በሶማሌ ክልል የኢንዱስትሪ ልማት ትኩረት እንዳልተሰጠው ጠቁመው፥ ለዚህም የኢንቨስትመንት ስበት ማነስ እና ሌሎች ጉዳዮችን በምክንያትነት አንስተዋል።
በቀጣይም የሶማሌ ክልል ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ለወደብ ያለውን ቅርበት ግምት ውስጥ ያስገባ የልማት ስራ ይካሄዳል ብለዋል።
አልሚ ባለሀብቶችም ሶማሌ ክልል በኢንዱስትሪው ዘርፍና ሌሎች ዘርፎች ላይ ያሉ ጸጋዎችን እንዲያለሙም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፥ አንድ አይነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት ለአገር ቀጣይነት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።
በመሰረተ ልማት፣ በግብዓትና በሰው ኃይል ትስስር ያደረጉ ዜጎች ያሏቸው አገራት እድገታቸውን ማስቀጠል እንደቻሉ ጠቁመው፥ በአገራችንም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጠንካራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ትስስር ያለው የኢኮኖሚ ስርዓት በመፍጠር ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲኖር በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከ27 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ በመፍጠር ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደተቻለ ተናግረዋል።
በየአመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ስራ እንደሚፈልጉ ገልጸው ኢንዱስትሪውም በስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲያንሰራሩ በማድረግ የገቢ ምርትን መተካት የተቻለበት ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
የገቢ ምርቶችን በመተካት ከሁለት ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚሆኑ የአገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ገበያ በማስገባት ሰፊ የስራ እድል እና የገበያ ማረጋጋት ስራ መከናወኑንም ተናግረዋል።
ወደ ውጭ ከተላከ እንጀራም ከ28 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደተቻለ አስታውቀዋል።