በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የውጭ ባለሀብቶች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል-ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የውጭ ባለሀብቶች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል-ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 18/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የውጭ ባለሀብቶች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ያለመ “ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023” ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በፎረሙ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ፤ ኢትዮጵያ ሰፊ መሰረተ ልማት፣ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ሎጅስቲክስ፣ ምቹ ፖሊሲ እና አሰራር እንዲሁም አምራች የሰው ኃይል ያላት በመሆኗ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ያደርጋታል ብለዋል።
በመሆኑም ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በግብርና፣ ማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ ኢነርጂ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፎች ባሉ ምቹ አማራጮች ሙዓለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስት በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከሆኑ ቀዳሚ ሀገራት መካከል አንዷ እንደሆነች ገልጸዋል።
መንግስት የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እና ቀጣይነት ያለው ምጣኔ ሀብት ለመገንባት የሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሀ ግብር በመተግበር ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
በምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሀ ግብሩ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ቅድሚያ እንደተሰጠው ጠቅሰው፤ ለዚህም የቴሌኮም፣ ፋይናንስና ሌሎች ዘርፎችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት በመደረግ ላይ ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ለግሉ ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት በአግባቡ በመጠቀም ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያሳይ አውደርዕይ በፎረሙ ቀርቧል።
ዛሬ በተጀመረው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በርካታ ባለሀብቶች፣ አምባሳደሮች፣ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች እና ሌሎችም ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን ፎረሙ ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት ይካሔዳል።