ቀጥታ፡

“ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023” ፎረም ተጀመረ

 

አዲስ አበባ ሚያዝያ 18/2015(ኢዜአ):-ዓለም አቀፍ የንግድ ተቋማትና ባለሃብቶች የሚሳተፉበት “ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023 ” ፎረም ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል መካሄድ ጀምሯል።

በፎረሙ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨሰትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ፣የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ፣ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች፣ዲፕሎማቶች፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ለሶስት ቀናት የሚቆየው ፎረም “በኢትዮጵያ ኢንቨት በማድረግ በልጽጉ - ማራኪ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሏት ምድር" በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል፡፡


 

ከመላው ዓለም የተወጣጡ ከ600 በላይ የንግድ ተቋማት ኃላፊዎችና ኢንቨስተሮች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ፎረሙ በኢትዮጵያ ያሉትንና ያልተነኩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለዓለም ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ተገልጿል።

መርሐ-ግብሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮ ቴሌኮም ዋና አጋር በመሆን እንዳዘጋጁት የተገለጸ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ የፎረሙ ሕጋዊ የጉዞ አጋር መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ከ600 በላይ አዳዲስ የውጭ ቀጥተኛ ባለሀብቶች እንደሚሳተፉበት በተገለጸው ፎረም በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ፈሰስ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም