ቀጥታ፡

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ

 

አዲስ አበባ ሚያዚያ 18/2015(ኢዜአ):-በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

አርባ ምንጭ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይጫወታሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ አርባ ምንጭ ከተማ በ22 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ45 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

አርባ ምንጭ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፏል፤ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም።

አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ ባህር ዳር ከተማ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስድስት ከፍ ያደርጋል።

ሁለቱ ክለቦች በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም በድሬዳዋ ስታዲየም በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ21ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር ፋሲል ከነማ ከሃዋሳ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ፋሲል ከነማ በ27 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሃዋሳ ከተማ በ31 ነጥብ 5ኛ ደረጃን ይዟል።

ፋሲል ከነማ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ አሸንፏል። ሶስት ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።

ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል፤አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም በድሬዳዋ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ21ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ሲዳማ ቡናን 3 ለ 1 ሲረታ ለገጣፎ ለገዳዲ ከሀዲያ ሆሳዕና ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም