ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የጋራ ትብብር እንዲጎለብት የሚኖራትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የጋራ ትብብር እንዲጎለብት የሚኖራትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 18/2015(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የጋራ ትብብር እንዲጎለብት የሚኖራትን ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ተናገሩ።
ሱዳን የገጠማትን ችግር በሰላማዊ መንገድ እንድትፈታ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም ተናግረዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ያሉበትን ሁኔታ የመከታተልና ደኅንነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
የሱዳን አለመረጋጋት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም ከውስጥ ሰላሟ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ኢትዮጵያ ሱዳን እንድትረጋጋ ትፈልጋለች ብለዋል።
"ኢትዮጵያ የምትጠቀመው የተረጋጋ ጎረቤት አገር ሲኖር ነው" ያሉት አምባሳደሩ በቀጣናው ንግድና ኢንቨስትመንት፣ ሰላምና ደኅንነት የሚረጋገጠውም የአካባቢው አገራት ሰላም ሲጠበቅ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማዕከልና የውጭ ግንኙነት ዋነኛ መርህም ከዚሁ የሚመነጭ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።
በመሆኑም አሁን ሱዳን የገጠማት ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የኢትዮጵያ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ለስኬቱም አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ሕዝብ ጎን እንደምትቆም በመግለጽ ከአንድ ወገን ጋር በመሰለፍ የምትወስደው አቋም እንደሌለ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የሱዳንን ሰላም ሂደት ሕዝቡ በባለቤትነት ሊመራው እንደሚገባ በጽኑ እንደምታምን ጠቁመዋል።
በሱዳን የውስጥ ጉዳይ የማንኛውም ሦስተኛ ወገን ጣልቃገብነት ችግሩን ከማባባስ በዘለለ ሌላ ፋይዳ እንደማይኖረው ኢትዮጵያ በግልጽ አቋም እያንጸባረቀች ነው ብለዋል።
በመሆኑም የሰላም ሂደቱ አሳታፊ በሆነ መልኩ ከዚህ ቀደም በተፈረመው የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ እልባት ሊያገኝ እንደሚገባ ኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል።
ለሱዳን ሕዝብም የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎች ለማድረግ ኢትዮጵያ ያሳየችው ቁርጠኝነት ያላትን ወዳጅነትና አጋርነት ለመግለጽ ነው ብለዋል።
ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ረዥም ድንበር የምትጋራ፤ ጠንካራ የባህል፣ የቋንቋ እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ያላት ጎረቤት አገር መሆኗንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ሁኔታ የመከታተልና ደኅንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች ሱዳን ከሚገኘው ኤምባሲ ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በሱዳን የሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች በግጭት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ዓለም አቀፍ ሕጎችና የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን ኃላፊነት እየተወጣች መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ጊዜያዊ የቆንጽላ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ መፈጠሩንና ሥራዎችን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የቆየውን ጦርነት የቋጨችበት ሂደት ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ማረጋገጫ የሰጠና አርዓያ በመሆኑ ሱዳኖች ሊማሩበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ያስተላለፉትን መልዕክት መተግበር ሱዳን ሰላሟን ማረጋገጥና ወደ ቀድሞ መረጋጋቷ መመለስ እንዳለባት ጠቁመዋል።