የትራንስፖርት ዘርፉን ቀልጣፋና ዘመናዊ በማድረግ የአደጋ ተጋላጭነትን መቀነስና አገልግሎቱን ማሳለጥ ይገባል- ዶክተር አለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
የትራንስፖርት ዘርፉን ቀልጣፋና ዘመናዊ በማድረግ የአደጋ ተጋላጭነትን መቀነስና አገልግሎቱን ማሳለጥ ይገባል- ዶክተር አለሙ ስሜ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 17 / 2015 (ኢዜአ) የትራንስፖርት ዘርፉን ቀልጣፋና ዘመናዊ በማድረግ የአደጋ ተጋላጭነትን መቀነስና አገልግሎቱን ማሳለጥ እንደሚገባ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ተናገሩ።
የመንገድ ደኅንነት የትራፊክ አደጋ አሁናዊ ሁኔታና የባለድርሻ አካላት ሚናን በማስመልከት በቢሾፍቱ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
የትራንስፖርት ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ እድገትና ልማት ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ በዘመናዊ አሠራር መደገፍ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በዘርፉ የጥራት፣ የፍትሃዊ ተደራሽነት፣ የአገልግሎት ክፍያ፣ የስነ-ምግባርና መሰል ችግሮችን በትብብር መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ኋላቀር የትራንስፖርት አገልግሎት የተሳለጠ ካለመሆኑ የተነሳ የአደጋ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
በመሆኑም የትራንስፖርት ዘርፉን በጋራ በማዘመን የአደጋ ተጋላጭነት ምጣኔን መቀነስና አገልግሎቱን የተሳለጠ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በተለይም የአሽከርካሪዎች የሙያ መጓደል ለትራፊክ አደጋ መንስኤ ከፍተኛውን ድርሻ መያዙን ጠቅሰው፤ የቁጥጥርና የሙያ ብቃት ምዘናውን ማዘመን ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ብለዋል።
ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በትብብር የሚሰራ መሆኑን ዶክተር አለሙ አረጋግጠዋል።
የመንገድ ደኅንነት እና መድህን ፈንድ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አባሱ፤ በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ በዓመት በአማካይ ከ4 እስከ 5 ሺህ ሰዎች ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንገድ ደኅንነት፣ የተሽከርካሪዎች ጥራት፣ የአሽከርካሪዎች የብቃት ማነስና የስነ-ምግባር ችግር የአደጋዎቹ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የዘርፉን ቁጥጥርና አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ተናግረው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ በክልሎች የቁጥጥር ሥርዓቱ የሚመራበት አሠራር ወጥነት የጎደለው በመሆኑ በሚፈለገው ልክ የተጠያቂነት ሥርዓት እንዳይሰፍን አድርጓል ብለዋል።
የአሠራር ማሻሻያዎችን በሁሉም ክልሎች በማስተግበር ረገድ የሚስተዋሉት ክፍተቶች ሊስተካከሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በዲጂታል የታገዘ የመረጃ ልውውጥ፣ የሰው ኃይል የብቃት ምዘና በተቆራረጠና ውጤታማነቱ በሚፈለገው ደረጃ ተደራሽ አለመሆኑም ቅንጅታዊ አሰራሩ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል ብለዋል።
የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በየወቅቱ ከሚሰሩ የዘመቻ ሥራዎች በዘለለ በተደራጀና ወጥነት ባለው መልኩ በትብብር መሥራትም ይገባል ነው ያሉት።
በመሆኑም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ክልሎች የማሻሻያ ሥራዎችን በማከናወን ረገድ በቁርጠኝነት ለመሥራት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።