ቀጥታ፡

የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት አህጉራዊ ትስስርን ለማጠናከር የግሉን ዘርፍ በኃይል ልማት ማሳተፍ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 17/2015 (ኢዜአ)፡ የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት አህጉራዊ ትስስርን ለማጠናከር የግሉን ዘርፍ በኃይል ልማት  በስፋት ማሳተፍ እንደሚገባ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።


 

'አፍሪካ ኢነርጂ ናው' በተሰኘው ድርጅት በተሰናዳው መድረክ ዓለም አቀፍ የግል ኩባንያዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና የሁለቱ ሀገራት የመንግሥትና የግል ዘርፍ ተወካዮች ታድመዋል። 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በውሃ፣ በፀሐይ፣ በነፋስ እና በጂኦ-ተርማል የኃይል አማራጮች በአጠቃላይ ከ300 እስከ 400 ጊጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አላት ብለዋል።

እነዚህ ሁሉ ዕድሎች እያሉ ግን አሁናዊ አቅሟ 5 ጊጋ ዋት መሆኑን ገልጸው፤ ይህን እምቅ አቅም ለመጠቀም ገንዘብና ቴክኖሎጂ ስለሚያስፈልግ ከመንግሥት ባሻገር የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአሥር ዓመቱ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ዜጎችን በስፋት የአሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የማድረግ ግብ መያዙን ገልጸው፤ ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ የቀጣናው ሀገራትን በኃይል የማስተሳሰር ዕቅድ ሰንቃ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ታንዛኒያም በታዳሽ ኃይል ዘርፍ እምቅ አቅም ያላት በመሆኗ በኢትዮ-ኬንያ የኃይል መስመር በማስተሳሰር እስከ ደቡብ አፍሪካ ያለውን ቀጣና በኃይል ልማት የማገናኘት ዕድል መኖሩን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያና ታንዛኒያ እምቅ የታዳሽ ኃይል አቅም ያላቸው በመሆኑ በጋራ ጥቅም ላይ መተባበር እንዳለባቸው ገልጸው፤ የግሉ ዘርፍ በኃይል ልማት ተሰማርቶ አፍሪካን እንዲያስተሳስር ጠይቀዋል።


 

የኢንቨስትመንት  ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፤ የፖሊሲና የሕግ ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር በኃይል ዘርፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ ከታዳሽ ኃይል 40 ቢሊየን ዶላር ለመሰብሰብ ግብ መቀመጡን ገልጸው፤ የዘርፉን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ የግሉን ዘርፍ በኃይል ልማትና ሥርጭት ማሳተፍ ትኩረት ተደርጓልም ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም የግል ኩባንያዎች በኃይል ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም እና ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር በመጠቀም መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የታንዛኒያ መንግሥት ተወካይ እና የሀገሪቱ የጂኦ-ተርማል ልማት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ማቲው መዋንጎምባ፤ ቀጣይነት ያለው ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ታዳሽ ኃይል ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያና ታንዛኒያ ያላቸውን እምቅ የታዳሽ ኃይል በትብብር በማልማት አፍሪካ በሃይል የማስተሳሰር አቅም ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የመድረኩ አዘጋጅ የሆነው 'አፍሪካ ኢነርጂ ናው' ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሞርስ ቫይግል፤ አፍሪካ እምቅ የኃይል አማራጮች ቢኖራትም እስካሁን በቅጡ ጥቅም ላይ አለማዋሏን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በቀጣይ በዘርፉ ለግሉ ባለሃብት ጭምር ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በመፍጠር በታዳሽ ኃይል ላይ በስፋት መሥራት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም