ቀጥታ፡

ኮርፖሬሽኑ የሰነድ አያያዝና አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታል ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 17/2015(ኢዜአ)፡- የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሰነድ አያያዝና አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታል ለማድረግ ከኢትዮጵያ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል እና የኢትዮጵያ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ደጋቶ ኩምቤ ስምምነቱን ፈርመዋል።

የኮርፖሬሽኑን አሠራር በማዘመን የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት ስምምነቱ የላቀ አስተዋጽዖ ያለው መሆኑን አቶ ረሻድ ገልጸዋል።

በአሠራር ሂደት አልፎ አልፎ ሐሰተኛ ሰነዶች ያጋጥሙ እንደነበር አስታውሰው፤ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጋር የተደረሰው ስምምነት ዓይነተኛ መፍትሔ ይሆናል ብለዋል።

የመረጃ ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን መደረጉ በተለይም በውክልና ውል የሚዋዋሉ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች የውክልና ተገቢነታቸውን ለማረጋገጥ ያስችላልም ነው ያሉት።

ከዚህ በተጨማሪ አሠራሩ በቴክኖሎጂ እንዲደግፍ መደረጉ የደንበኞችን ጊዜ እና ጉልበት ለመቆጠብ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ደጋቶ ኩምቤ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ከሽያጭ፣ ከገንዘብ እና ባለቤትነትን ከማስተላለፍ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ወደ ዘመናዊ አሠራር ለማስገባት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ሐሰተኛ ማስረጃን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም ሕገ-ወጥነትን ለማስቀረት የዲጂታላይዜሽን ሥራው የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።

ከዛሬ  ጀምሮ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች በአካል መሄድ ሳይጠበቅባቸው በአገልግሎቱ በዲጂታል የመረጃ ቋት አማካኝነት የሚፈልጉትን መረጃ ማግኘትና ማረጋገጥ እንደሚችሉ ተፈቅዶላቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት መሰል አገልግሎቶችን ለሌሎች ተቋማት እየሰጠ እንደሚገኝም ተመልክቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም