ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት አማካይነት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ26 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

ጅግጅጋ፣ ሚያዝያ 17 / 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት አማካይነት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ26 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ተገለጸ። 

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም መድረክ  ዛሬ  በጅግጅጋ ተካሂዷል። 

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ በመድረኩ ላይ እንዳስታወቁት፤ በኢንተርፕራዞች ተመርቶ ወደ ውጭ ለመላክ ከታቀደው ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያስገኙ ምርቶች በማቅረብ ውጤታማ  ሆኗል። 


 

ገቢው ከጨርቃ ጨርቅ፣ ከአልባሳት ውጤቶች፣ የቆዳ ውጤቶችና የጫማ ስራ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ ውጤቶች የዕድ-ጥበብ ውጤቶች ኬሚካልና ማዕድን ውጤቶች መገኘቱንም አስረድተዋል። 

አዲስ በተቋቋሙና ነባር ኢንተርፕራይዞች 87 ሺህ 740 ሰዎች የስራ እድል መፈጠሩን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የካፒታል ዕቃዎች መሰራጨታቸውን ገልጸዋል። 

የሶማሌ ክልል የክህሎትና ስራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ጋይድ በክልሉ ኢንተርፕራይዞች እንዲጠናከሩ ከፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ጋር እንዲተሳሰሩ መደረጉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሙያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ በጅግጅጋ ከተማ  በ120 ሚሊዮን ብር ወጪ የተቋቋመው ሳሂድ የብረታ ብረት አምራች ኢንዱስትሪ ለ345 ወጣቶች ሥራ መፍጠሩን ለአብነት አቅርበዋል። 

የመድረኩ ተሳታፊዎች በጅግጅጋ ከተማ በኢንዱስትሪና በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም