በኢንዱስትሪው ዘርፍ በዘጠኝ ወራት ከ160 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪው ዘርፍ በዘጠኝ ወራት ከ160 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሚያዚያ 17/2015(ኢዜአ)፡-በኢንዱስትሪው ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ160 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በማስመልከት ከቀናት በኋላ በእንጦጦ ፓርክ የሚካሄደውን የሩጫ ውድድር በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አገሪቷን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ዓላማ ማድረጉን ጠቅሰው ለዚህም ሚያዚያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም በእንጦጦ ፓርክ ሩጫ ውድድር ይካሄዳል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ባህል መገንባት፣ የኢንዱስትሪ መሰረትን ማስፋት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ችግሮችን መፍታት የንቅናቄው ዓላማ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ በአንድ ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ስራ አቁመው ከነበሩ ኢንዱስትሪዎች መካከል ከ300 የሚልቁት ዳግም ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ161 ሺህ በላይ ዜጎች በዘርፉ የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ለማጠናከር ከ3 ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር በእንጦጦ ፓርክ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
ለኢንዱስትሪ እንሩጥ በሚል በሚካሄደው ውድድር ባለሃብቶች፣ አትሌቶች እና ሌሎችም ግለሰቦች ይሳተፋሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአገር አቀፍ ደረጃ ሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይፋ መደረጉ ይታወቃል።