ቀጥታ፡

"ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት አለኝታ በመሆን አኩሪ ተግባር የፈጸማችሁ ሁሉ የላቀ ክብርና ምስጋና ይገባችኋል"- ሌተናል ጄነራል አለምሸት ደግፌ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2015 (ኢዜአ)፦ "ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት አለኝታ በመሆን አኩሪ ተግባር የፈጸማችሁ ሁሉ የላቀ ክብርና ምስጋና ይገባችኋል" ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና ተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄነራል አለምሸት ደግፌ ገለጹ።

በአገራዊ ግዳጅ የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱ የቀድሞ ሠራዊት አባላት በዛሬው እለት እውቅና እና የክብር ሽኝት ተደርጎላቸዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና ተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄነራል አለምሸት ደግፌ፤ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ኢትዮጵያ በጠራቻቸው ጊዜ ፈጣን ምላሽ በመስጠት አኩሪ ተግባር መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

"በዚህም ለአገራችሁ ስትሉ አኩሪ ተግባር የፈጸማችሁ ሁሉ የላቀ ክብርና ምስጋና ይገባችኋል" ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑንና ክብሯን የሚያስጠብቅ አስተማማኝ ሠራዊት መገንባቱንም ጠቅሰዋል።

ለሠራዊቱ ግንባታ በተለይም የቀድሞ ሠራዊት አባላት የላቀ ተሳትፎ እንደነበራቸው አስታውሰው፤ ለዚህም የላቀ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በክብር የተሸኙት የቀድሞ ሠራዊት አባላት በሚመለሱባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሰላምን በማጽናት  ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል። 


 

በክብር ከተሸኙ የቀድሞው ሠራዊት አባላት መካከል ኮለኔል ደማ ወልደማርያም፣ ሻምበል ንጉሴ ፈረደ እና ሻምበል ፋሲል አስማረ በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ ባበረከቱት አስተዋጽዖ ሁሉ ክብርና ኩራት የሚሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ሀገር በምትፈልግባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠው ለተሰጣቸው እውቅና እና የላቀ ምስጋና አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ ሰላም፣ የጋራ ልማትና አብሮነት በቀጣይ የህይወት ዘመናቸውም አበርክቷቸውን የማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም