ቀጥታ፡

 በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ  ከ350 በላይ ኢንዱስትሪዎች ዳግም ስራ ጀምረዋል- ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሚያዚያ 17/2015 (ኢዜአ)፡-በተለያዩ ምክንያቶች ስራ አቁመው የነበሩ ከ350 በላይ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዳግም ስራ መጀመራቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው 14ኛ መደበኛ ጉባኤ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤታማነት፣ የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነት፣ የግብአት አቅርቦት፣ የስራ እድል ፈጠራና ኢንዱስትሪዎች የሚገነቡበት አካባቢ ፍትሐዊነት ይገኙበታል።

ሚኒስትሩ በኢንዲስትሪው ዘርፍ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። 


 

ለአብነትም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ቅንጅታዊ አሰራርን የማጎልበት፣የፖሊሲ ማሻሻያ የማድረግና ስትራቴጂዎች የማውጣት ስራዎች ጠቅሰዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝና ጸጥታ ችግር ሳቢያ ስራ አቁመው የነበሩ ከ350 በላይ ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ስራ መመለሳቸውን አቶ መላኩ የገለጹት።

ባለፉት 21 ዓመታት በስራ ላይ ሲተገበር የቆየውና ከፍትሐዊነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን ለመመለስ ማነቆ የነበረው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ እየተደረገበት ነው ብለዋል።

ከኢንቨስትመንት ፍሰት ጋር በተያያዘም ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በዘርፉ የመሰማራት ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉን የምጣኔ ሃብት እድገት ለማሳደግ የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም