ቀጥታ፡

ጥራትና ደህንነታቸው ያልተጠበቀ የምግብና የመድሃኒት ምርቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ሙያተኞች ጋር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ጅማ ሚያዝያ 17/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ጥራትና ደህንነታቸው ያልተጠበቀ የምግብና የመድሃኒት ምርቶችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ከመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ሙያተኞች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ከጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም ከምዕራብ ኦሮሚያ ለተውጣጡ የሚዲያ ሙያተኞች ጥራትና ደህንነታቸው ያልተጠበቀ ምግብና መድሃኒት ላይ ያተኮረ የሁለት ቀን ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ነው።


 

በስልጠናው በማንኛውም ማስታወቂያ የተከለከሉ ምርቶችን ከመከላከልና ህገወጥ የመድሃኒት ዝውውር በህብረተሰብ ጤና ላይ ያለውን ተጽእኖ ማሳየት እና ማስገንዘብ እንደሆነም ተገልጿል።

የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበራ ደነቀው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ጥራትና ደህንነቱ ያልተጠበቀ ምግብና መድሃኒት እንዲሁም የመዋቢያ ምርቶችን ለመቆጣጠርና መከላከል እንዲያስችል መረጃን በተገቢው መልኩ ማድረስ ይገባል።

ሕብረተሰቡ ለመድሃኒት፣ ለምግብነት እና ለመዋቢያነት የሚጠቀመው ምርት ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የመረጃ ተደራሽነት ወሳኝ መሆኑንም አክለዋል።

የዚህ ስልጠና ዋና አላማም የሚዲያ ባለሞያዎች ጉዳቱን ተረድተው ሕብረተሰቡን እንዲያስገነዝቡ ማስቻል ነው ብለዋል።

ባለስልጣኑ ማንኛውም ሰው ጥራቱ፣ ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድሃኒትንና የምግብ ምርቶችን በመጠቀም ጤናው የተጠበቀ እንዲሆን ከመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች ጋር በቅርበት እየተሰራ ነውም ብለዋል።

የአልኮል መጠጦችን እና የትምባሆ ምርቶችን አስመልክቶ የሚሰሩ የማስታወቂያና ተያያዥ ስራዎችን በተመለከተም ሙያተኞቹ በቂ ግንባዜና እውቀት እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

የባለስልጣኑ የጅማ ቅርንጫፍ ሀላፊ አቶ ሚፍታ ዝናብ በበኩላቸው ሰዎች በገንዘባቸው ገዝተውት የሚጠቀሙት የምግብና የመድሀኒት እንዲሁም ተያያዥ ምርቶች በጤናቸው ላይ ጉዳት እንደማያስከትል ማረጋገጥ እንዳለባቸው ማሳወቅ ይገባል ነው ያሉት።

ይህንንም ማድረግ የሚቻለው በየአካባቢው ያሉ መገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ሙያተኞችን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም