ምክር ቤቱ አዲስ የተሻሻለውን የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ አዲስ የተሻሻለውን የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ አጸደቀ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2015 (ኢዜአ) ፦የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመከላከያ ሰራዊትን የሪፎርም ስራዎች ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ አዲስ የተሻሻለውን አዋጅ አጸደቀ።
የመከላከያ ሰራዊት አዋጅን በተመለከተ በውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል።
የረቂቅ አዋጁን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ያቀረቡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ኖጎ፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተደረጉ ማሻሸያዎችና የተጨመሩ አዳዲስ ጉዳዮችን ዘርዝረዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ እያከናወነ ካለው የሪፎርም ስራዎች ታሳቢ ያደረገ የህግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ የአዋጅ ማሻሸያው መደረጉን አብራተዋል።
መከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለውን የሪፎርም ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲረዳው የጡረታ እድሜ አወሳሰንና የጡረታ እድሜ ማራዘም፣ የሰራዊቱ መብት፣ ጥቅማጥቅምና ሌሎችም በማሻሻያ አዋጁ ውስጥ ተካተዋል።
ማሻሻያ ከተደረገባቸው አንቀጾች ውስጥ ሰላሳ አመትና ከዛ በላይ ያገለገሉ የሰራዊት አባላት የግል መኖሪያ ቤት የሌላቸው መሆኑ ሲረጋገጥ የግል መኖሪያ ቤት ወይንም የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲያገኙ መንግስት እንደሚያመቻችም ተደንግጓል።
የቋሚ ኮሚቴውን ሪፖርት በማድመጥ የተወያየው ምክር ቤቱ አዲስ የተሻሻለውን የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ አጽድቆታል።
የምክር ቤት አባላት የቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መነሻ በማድረግ የመኖሪያ ቤት ወይንም የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታና በሌሎች በረቂቅ አዋጁ የተካተቱ ድንጋዴዎች ላይ ጥያቄና አስተያየቶችን አቅርበዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ በስራ ላይ ያሉና ሰራዊቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አማራጮችን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የህብረ ብሄራዊ ሰራዊት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የአዋጁ መጽደቅ ለዚህና ሌሎች ስራዎችም የላቀ ሚና የኖረዋል ብለዋል።
"በምክር ቤቱ 14ኛ መደበኛ ስብሰባ በአጀንዳነት ይዟቸው ከነበሩት መካከል "የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ማጽደቅና" እና "የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል" የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራት የሚሉ አጀንዳዎችን ለቀጣይ መደበኛ ስብሰባው አዘዋውሯል።