የጸረ-ተዋህሲያን መድኃኒት መላመድ የዓለም የጤና ስጋት ሆኗል-ዓለም ጤና ድርጅት - ኢዜአ አማርኛ
የጸረ-ተዋህሲያን መድኃኒት መላመድ የዓለም የጤና ስጋት ሆኗል-ዓለም ጤና ድርጅት
አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2015 (ኢዜአ) የጸረ-ተዋህሲያን መድኃኒት መላመድ የዓለም የጤና ስጋት መሆኑን በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ኖህላላ ድላሚኒ ተናገሩ።
የዓለም ጤና ድርጅት ከተመረጡ የአፍሪካ አገራት የመጡ ባለሙያዎችን ያሳተፈ በጸረ-ተዋህሲያን መድኃኒት መላመድን መከላከል ላይ ያተኮረ ጉባኤ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
ጉባኤው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ 12 የአፍሪካ አገራት የመጡ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ኖህላላ ድላሚኒ፤ የጸረ-ተዋህሲያን መድኃኒት መላመድ አድፍጦ እንደሚፈነዳ ወረርሺኝ በከፍተኛ ደረጃ የዓለም የጤና ስጋት ሆኗል።
መድኃኒትን ያለአግባብና ከሚፈለገው መጠን በላይ መጠቀም የጸረ-ተዋህሲያን መድኃኒት መላመድ መንስኤ መሆኑን ገልጸዋል።
ችግሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልቶ የወጣ ቢሆንም በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
የጸረ-ተዋህሲያን መድኃኒት መላመድ በአገራት የጤና፣የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ መስተጋብር ላይ ቀውስ እያስከተለ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ጉዳቱን ለመቀነስ የተቋማት ቅንጅት አስፈላጊ በመሆኑ ምሁራን፣ መንግስትና የግሉ ዘርፍ በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፤ በኢትዮጵያ የጸረ-ተዋህሲያን መድኃኒት መላመድን ለመከላከል በ100 የጤና ተቋማት ላይ በተለየ ሁኔታ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዜጎች መድኃኒቶችን ከሐኪም ትዕዛዝ ውጭ እንዳይጠቀሙ፣ መድሃኒት ቤቶች ካለ ማዘዥ እንዳይሸጡ፣ ታማሚዎች የታዘዘላቸውን መድኃኒት በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በኮንትሮባንድ የሚገቡ መድሃኒቶችን መከላከልና በተፈቀደለት መድኃኒት አስመጪ ብቻ እየገባ መሆኑን የመቆጣጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጸረ-ተዋህሲያን መድኃኒት መላመድን ለመከላከል ኢትዮጵያ አገር አቀፍ የድርጊት መርሃ ግብር አውጥታ እየሰራች ስለመሆኑም ጠቅስዋል።
በጉባኤው ከቡርኪናፋሶ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋና፣ ኬኒያ፣ ላይቤሪያ፣ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሴራሊዮን፣ ታንዛኒያ፣ ከዛምቢያ እና ዚምባቡዌ የመጡ ባለሙያዎች በጉባኤው እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በሽታ አምጪ የሆኑ ጀርም፣ቫይረስ፣ ፈንገስ ያሉ በሰው እና በእንስሳት ጤና ላይ እክል የሚፈጥሩ ተዋህሲያን ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ጸረ-ተዋህሲያን ደግሞ እነዚህን ለመከላከል የሚወሰዱ መድኃኒቶች መሆናቸው ይታወቃል።