በደቡብ ክልል በሴቶች ተሳትፎ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዢ ለማከናወን እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል በሴቶች ተሳትፎ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዢ ለማከናወን እየተሰራ ነው
ዲላ ሚያዚያ 17 / 2015 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ክልል በሴቶች ተሳትፎ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዢ ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል የሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የሴቶች የቦንድ ግዢ የንቅናቄ መድረክ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ወላይቴ ቢተው እንደተናገሩት፤ የክልሉ ሴቶች ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ይህንን ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠል በክልል ደረጃ ለአንድ ወር የሚቆይ የቦንድ ሽያጭ ዘመቻ መጀመሩን አስረድተዋል።
በዚህም የክልል ማዕከልን ጨምሮ ከ17 የዞንና ከልዩ ወረዳ መዋቅሮች ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጸዋል።
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሴቶች በቦንድ ግዥው በነቂስ እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት እቅዱን ለማሳካትም ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የጌዴኦ ዞን የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደሪቤ ጃኖ በበኩላቸው የዞኑን ማህበረሰብ በማስተባበር ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በሂደቱ የሴቶች ተሳትፎ የላቀ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ ከሀገራዊ ፋይዳው ባለፈ የሴቶችን የቁጠባ ባህል በማሳደግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የጌዴኦ ዞን ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ለምለም ከበደ ናቸው።
የዞኑ ሴቶች ቦንድ በመግዛትና አሻራቸውን በማስቀመጥ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
ሴቶች የግድቡ ለሀገር ያለውን ጥቅም በመረዳት ድጋፋቸውን በቁርጠኝነት አጠናክረው እያስቀጠሉ እንደሚገኙ የጠቀሱት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የጌዴኦ ዞን ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ነፃነት በቀለ ናቸው።
በዘመቻው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በቦንድ ግዥ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱን ነው የተናገሩት።
በመድረኩ የቦንድ ሽያጭ የተከናወነ ሲሆን የክልልና የዞን የሴቶች አደረጃጀት፣ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።