በአማራ ክልል ባሉ ሰፊና ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ኩባንያዎች በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ባሉ ሰፊና ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ኩባንያዎች በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ
አዲሰ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2015(ኢዜአ):-በአማራ ክልል ባሉ ሰፊና ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ኩባንያዎች በስፋት እንዲሳተፉ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጥሪ አቀረቡ።
"በረንታ ሲሚንቶ" የተሰኘው ሀገር በቀል ኩባንያ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ስመጥር ከሆነው 'ሲኤንቢኤም ግሩፕ' ከተባለ የቻይና ዓለም አቀፍ ኩባንያ አካል ከሆነው 'ሲኖማ ሲሚንቶ' የአጋርነት ስምምነት ፈጽመዋል።
መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እንዳሉት፤ ለኢትዮጵያ የክፉ ቀን ባለውለታ የሆነችው የቻይና ኩባንያዎች lኢትዮጵያ ዕድገት ሁነኛ ሚና እየተጫወቱ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በግንባታ ግብዓቶች ምርት ግንባር ቀደም የሆነው ሲኖማ ሲሚንቶ ወደ ከበረንታ ሲሚንቶ ጋር መስራቱ ለክልሉ እና ለሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ዕድሎች እንደሚያመጣ ገልጸዋል።
የበረንታ ሲሚንቶ በክልሉ የመጀመሪያው የሲሚንቶ ፋብሪካ በመሆኑ ፋብሪካው በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ምርት እንዲገባ በክልሉ ህዝብና መንግስት በጉጉት የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
የሁለቱ ኩባንያዎች ስምምነት በቴክኖሎጂና ዕውቅት ሸግግር ባሻገር በስራ ዕድል ፈጠራም ጉልህ ሚና የሚያበረክት እንደሆነ ነው የገለጹት።
ሌሎች የቻይና ኩባንያዎችም ማዕድንን ጨምሮ በርካታ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ባሉት አማራ ክልል ገብተው እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበው፤ የክልሉ መንግስትም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂኔር ሀብታሙ ተገኝ፤ የሁለቱ ኩባንያዎች መፈራረም በዘርፉ ለቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር በማመጣት ሲሚንቶን ጨምሮ ለግንባታው ግብዓት አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት ያግዛል ብለዋል።
በግንባታ ላይ ያልው በረንታ ሲሚንቶ በማምረት አቅሙ ትልቁ ፋብሪካ እንደሚሆን ጠቅሰው፤ በግንባታ ላይ የሚገኙት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሲጠናቀቁ የሲሚንቶ ሀገራዊ እቅርቦት ክፍተት እንደሚቀረፍ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተፈጠረው አሁናዊ ሰላም ለዘርፉ መነቃቃት ሌላው ዕድል መሆኑን ጠቅሰው፤ ዕምቅ የማዕድን ሀብት ባለው የዓባይ ሸለቆ ሌሎች ኩባንያዎችን እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛሆ ዚዩዋን በበኩላቸው 50 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮ-ቻይና ፖለቲካዊ ግንኙነት በመተማመንና ሁለትዮሽ ጥቅም ተመስርቶ ኢኮኖሚያዊና የንግድ ትስስር እምርታ አምጥቷል ብለዋል።
በቀጣይም ሌሎች በርካታ የቻይና ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንዱስትሪ፣ በግብርናው፣ በማመረቻው፣ በማዕድንና ሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ለዚህ ምቹ ሁኔታዎችንና የኢንቨስትመንት ድጋፎችን ማደረጉን አጠናክሮ እነዲቀጥል ጠይቀዋል።
የበረንታ ሲሚንቶ ፕሬጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢረሳው ምናሉ እና የሲኖማ ሲሚንቶ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዊ ሩሻን፤ ስምምነቱ ቀጣይነት ያለው ትብብና እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።
የግንባታ ግብዓት ማምረቻ የኢንዱስትሪ ፓርክ በማልማት የገበያውን ክፍተት ለመሙላት እና የካፒታል፣ የልምድና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ሸግግር በመፍጠር የሁለትዮሽ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቁርጠኛ እንደሆኑም ገልጸዋል።
"ቤአኤካ ጠቅላላ ቢዝነስ ግሩፕ" እና "ጀር" በተሰኙ ኩባንያዎች ጥምረት የተቋቋመው በረንታ ሲሚንቶ በምስራቅ ጎጃም ዞን በሸበል በረንታ ወረዳ በአባይ ወንዝ ሸለቆ ውስጥ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ለማምረት በግንባታ ላይ ይገኛል።
የቻይና በቀሉ 'ሲኖማ ሲሚንቶ' ደግሞ በ76 የዓለም ሀገራት ኢንቨስመንቱን ያስፋፋው 'ሲኤንቢኤም' ግሩፕ የተሰኘው የግንባታ ዕቃዎች አምራች ስመ ጥር ኩባንያ አካል ነው።