ቀጥታ፡

ከ250 በላይ የውጭ ሀገራት ና የሀገር ውስጥ   ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የንግድ ትርዒት ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ  ሚያዝያ 17/2015 (ኢዜአ)  ከ250 በላይ የውጭ ሀገራት ና የሀገር ውስጥ  ኩባንያዎች የሚሳተፉበት 13ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሊካሄድ ነው።

የኢትዮጵያ የንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ  ውቤ መንግሥቱ፤ የንግድ ትርዒቱን በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ለ13ኛ ጊዜ የሚካሄደው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከሚያዝያ 19 እስከ  23 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

በንግድ ትርዒቱ ከ250 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ስምንት የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች ይገኙበታል ነው ያሉት።

ከአገር ውስጥ ተሳታፊዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች ሲሆኑ 40 በመቶው ደግሞ በመካከለኛና በአነስተኛ ደረጃ የሚገኙ ናቸው ተብሏል።

ከውጭ ሀገራት ተሳታፊ ኩባንያዎች መካከልም የቻይና፣ ሱዳን፣ አልጄሪያና ሌሎችም መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የተለያዩ የውጭ አገራት ኩባንያዎች መሳተፋቸውም የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል።

13ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት "የኢትዮጵያን ይግዙ " በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም