ቀጥታ፡

ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠት ለሚለው አህጉራዊ መርህ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን የፈታችበት መንገድ ሁነኛ ተምሳሌት ነው--አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

 

አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2015(ኢዜአ)፦ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠት ለሚለው አህጉራዊ መርህ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን የፈታችበት መንገድ ሁነኛ ተምሳሌት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

አምባሳደር ምስጋኑ ከአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ፣ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ወቅት አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ሰላም የአፍሪካ ህብረት ያደረገውን ድጋፍ በማድነቅ ፤ በአፍሪካ የሚፈጠሩ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታትን መተማመን ያሳየ ነው ብለዋል ።


 

የኢትዮጵያ መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች የአፍሪካ ህብረት ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ያስቻለ አጋጣሚ ነበርም ብለዋል።

በዚህም አባል አገራት እና የአፍሪካ ህብረት አጋሮች ለተቋሙ ያላቸው እምነት እንዲጠናከር ማስቻሉንም ተናግረዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ የፓን አፍሪካ ዕሴቶች እንዲጠናከሩ ወደፊት በአፍሪካ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ዘዴ በማጎልበት ኢትዮጵያ እንደምሳሌ የምትወሰድ አገር ነች ብለዋል።

በማንኛውም የሰላም ውይይት የአፍሪካ ህብረት ሀሳብ የሚታይበት ማዕቀፍ እንዲሰፋ መስራት እንደሚገባ ሚኒስትር ዲኤታው አንስተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ ፣ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ የአፍሪካን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሀገራት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

አምባሳደር ባንኮሌ የኢትዮጵያ መንግስት ለወሰዳቸው እርምጃዎች ትልቅ አክብሮት እንዳላቸው ተናግረው የሽግግር ፍትህ እንዲፈፀም በመንግሥት በኩል ለሚደረገው ጥረት የአፍሪካ ህብረት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ ሱዳናውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የመፍታት አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል።

በተፈጠረው ችግር ምክንያት በካርቱም እና በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የውጭ አገራት ዜጎችን ለማገዝ እና ትብብር ለመስጠት ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

የሱዳንን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት እና የትብብር ፍላጎቶችን ለመመለስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤምባሲዎች የሚጠይቋቸውን ጉዳዮች ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ለኮሚሽነሩ አስረድተዋል ።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም