ቀጥታ፡

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 17/2015 ዓ.ም (ኢዜአ)፡- ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ለገጣፎ ለገዳዲ በ10 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና በ30 ነጥብ 5ኛ ደረጃን ይዟል።

ለገጣፎ ለገዳዲ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

ሶስት ጊዜ ተሸንፏል አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕና ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ አሸንፏል ሁለት ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።

ሁለቱ ክለቦች በሕዳር ወር 2015 ዓ.ም ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር የሊጉ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ21ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሐግብር አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አዳማ ከተማ በ27 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ሲዳማ ቡና በ21 ነጥብ 14ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

አዳማ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል።

በአንጻሩ ሲዳማ ቡና ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ሶስት ጊዜ ተሸንፏል ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በሕዳር ወር 2015 ዓ.ም ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ሲዳማ ቡና 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርሐግብር እስከ ሚያዚያ 20 2015 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም