የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ባለፉት ሶስት ወራት ያከናወናቸውን አበረታች ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ባለፉት ሶስት ወራት ያከናወናቸውን አበረታች ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ ሚያዝያ 16/2015(ኢዜአ) የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ባለፉት ሶስት ወራት ያከናወናቸው አበረታች ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የብሔራዊ የተሀድሶ ኮሚሽን ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የሰላም ሚንስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱአለም ገለጹ፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸም በዛሬው እለት ተገምግሟል።
በመድረኩም የሰላም ሚንስቴር በበላይነት የሚመራው የብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ምክር ቤት ያከናወናቸውን ተግባራት ግምገማና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በዚህም ኮሚሽኑ የአደረጃጀት እንዲሁም የሰው ሀይል እና ስምሪት የመጨረሻ ረቂቅ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
ኮሚሽኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ሥራ ለመግባት የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረሱም ነው የተገለጸው፡፡
የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ኮሚሽኑ ከክልሎች ጋር ባደረገው ውይይት የኮሚሽኑ ተልዕኮ ላይ በተሻለ መልኩ ግልፅነትና መግባባት መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት ወራት በዋናነት ያከናወናቸው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አበረታች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ኮሚሽኑ ከክልሎች ጋር ያደረጋቸውን ውጤታማ ውይይቶች ወደ ህዝቡ ለማስፋት መስራት እንዳለበትም አመላክተዋል።
ኮሚሽኑ በቀጣይም የሰበሰባቸውን መረጃዎች የማጥራት እና የማመሳከር ስራዎችን ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኮሚሽኑ ስራ የበርካታ አካላትን ቅንጅት የሚጠይቅ መሆኑን ያነሱት ሰብሳቢው፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ስራዎች እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ኮሚሽኑ የተቋቋመው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የትጥቅ አማራጭን በመከተል ከመንግሥት ጋር ሲዋጉ የነበሩ ተዋጊዎች በውይይት እና ድርድር ወደ ሰላም በማምጣት ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ መሥራት እንደሆነም የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ገልጸዋል።
የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በበኩላቸው ኮሚሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ስራዎች መስራቱን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑን በቀጣይ በመቀሌ ቅርንጫፍ ለመክፈት እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመው፤ ለዚህ የሚያስፈልግ የሰው ኃይል የማሟላት ስራ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡
በትግራይ ክልል የቡድን መሣሪያ የማስፈታት ሥራ የተጀመረ ሲሆን ይህ ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት፤ ክልሎች የኮሚሽኑን ስራ በማገዝ ረገድ የጀመሩትን ሚና አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
መረጃዎችን በማደራጀት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች መለየት እንደሚገባ አመላክተዋል።