በክፍያ መንገድ አስተዳደርና ደኅንነት የሚስተዋሉ ችግሮች በፍጥነት ሊስተካከሉ ይገባል- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በክፍያ መንገድ አስተዳደርና ደኅንነት የሚስተዋሉ ችግሮች በፍጥነት ሊስተካከሉ ይገባል- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
አዲስ አበባ ሚያዝያ 16/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በመንገድ አስተዳደርና ደኅንነት የሚስተዋሉ ችግሮችን እንዲያስተካክል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንተርፕራይዙ የ2013/14 የክዋኔ አዲት ሪፖርት ላይ ውይይት አድርጓል።
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በመንገድ አስተዳደር፣ ጥገና፣ ክብደት ቁጥጥር፣ የፍጥነት መቆጣጠር፣ የመንግሥት ግዥ መመሪያ አተገባበር፣ ሌሎች ችግሮች እንዳሉበት የዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝቱ አመላክቷል።
በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በመንገዱ ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና ብልሽት በወቅቱ ጥገና አለመደረጉም የኦዲት ሪፖርቱ ያሳያል።
በተመሳሳይ በክፍያ መንገዶች የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ዘመናዊ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ሥርዓት አለመዘርጋቱም የኦዲት ግኝቱ ያመላከተ ሲሆን የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎችን ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል።
በኦዲት ግኝቱ መሰረት የተወሰዱና በሂደት ላይ ያሉ የማስተካከያ እርምጃዎች ላይ የተቋሙ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሙስጠፋ አባሲመል በሰጡት ምላሽ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ አሰራሮች እየተዘረጉ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በመንገዶች ላይ እየደረሰ ባለው ጉዳት ላይም ለተነሱ ጥያቄዎች የኢንተርፕራይይዙ ምክትል ስራ አስኪያጅ አብይ ወረታው ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህም ጉዳት የደረሰባቸውን የመንገድ መሰረተ ልማቶች ለመጠገን ተቋሙ በራሱ አቅም ወርክሾፖችን በማደራጀት እየሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
የፌደራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ከግዥ መመሪያ፣ ከተፈቀደው ጭነት በላይ መጫን፣ በፍጥነት ወሰንና ሌሎች የመንገድ የመንገድ አስተዳደር ላይ የታዩ የኦዲት ግኝቶችን በቀጣይ በትኩረት ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ የፈሰሰባቸውንና እንቅስቃሴን የሚያሳልጡ መንገዶችን በተገቢ ማስተዳደር ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም ኢንተርፕራይዙ በመንገድ አስተዳደርና ደህንነት በኦዲት ግኝቱ የተገኙ ችግርችን በማረም ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቅ አሳስበዋል።
በመንገድ ጥገና፣ ክብደት ቁጥጥር፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ጉዳትና ስርቆት ላይ የሚስተዋሉ ችግርችን ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ ወደ ውስጥ በማየት ማስተካከል እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል፡፡