በዩኒቨርሲቲዎች ከስርአተ ምግብ ስልጠና ጋር ድንገተኛ የስነ-ምግብ ትምህርትን አካቶ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዩኒቨርሲቲዎች ከስርአተ ምግብ ስልጠና ጋር ድንገተኛ የስነ-ምግብ ትምህርትን አካቶ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው
ባህር ዳር ሚያዝያ 16/2015(ኢዜአ):- በዩኒቨርሲቲዎች ከስርአተ ምግብ ስልጠና ጋር ድንገተኛ የስነ-ምግብ ትምህርትን አካቶ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በመንግስት 14 ዩኒቨርሲቲዎች ድንገተኛ ስነ-ምግብ ትምህርትን በመደበኛነት መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።
ድንገተኛ የስነ-ምግብ ትምህርት በድርቅ፣ በሰው ሰራሽ ችግሮችና በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው ለምግብ እጥረት የተዳረጉ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
ትምህርቱ የስርዓተ-ምግብ ስልጠና የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች ለሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎቻቸው ከስልጠናው ጋር አያይዘው በኮርስ ደረጃ እንደሚሰጥ ተመላክቷል።
በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የድንገተኛ ስነ-ምግብ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብሩክ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ድንገተኛ የስነ-ምግብ ትምህርት በስርዓተ ምግብ ስልጠና ውስጥ ተካቶ መሰጠቱ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ያግዛል።
ከዚህ ቀደም የስርዓተ-ምግብ ስልጠና የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች ቢኖሩም፤ ድንገተኛ ስርዓተ-ምግብን በተመለከተ ተለይቶ ትምህርት ሲሰጥ እንዳልነበር አስታውሰዋል።
በዚህም የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙ ቀጥታ የሚመለከታቸውን ባለሙያዎችን ፈጥኖ በማሰማራት በኩል ችግር ነበር ብለዋል።
"በዩኒቨርሲቲዎች በመደበኛነት ትምህርቱ እንዲሰጥ መደረጉ የድንገተኛ ስነ ምግብ ባለሙያዎች እንዲኖሩ ከማድረግ ባለፈ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት ለምግብ እጦት የሚዳረጉ ዜጎችን በተለይም ሴቶች፣ ሕጻናትንና አረጋዊያን ፈጥኖ ለመታደግ ያስችላል" ብለዋል።
አቶ ብሩክ እንዳሉት፤ ስልጠናው እንዲጀመር የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአጋርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እየሰሩ ይገኛሉ።
በቢዩልዲንግ ሪዝሊያንስ ኢትዮጵያ ኦክስፎርድ ፖሊሲ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ ክስተቶች መሪ ዶክተር አያና የኔአባት በበኩላቸው "በኢትዮጵያ የስርዓተ-ምግብ ስልጠና የሚሰጡ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የድንገተኛ ስነ-ምግብ ትምህርትን አካተው እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ ነው" ብለዋል።
ትምህርቱ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሐረማያና ሰመራን ጨምሮ በ14 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ወጥ በሆነ አግባብ ከስርዓተ-ምግብ ስልጠና ጋር ተጣምሮ እንደ አንድ ኮርስ እንደሚሰጥም አመልክተዋል።
ለዚህም ለማስተማሪያ የሚያገለግሉ ሰነዶች በዘርፉ ምሁራን መዘጋጀታቸውን ነው የጠቆሙት።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስማማው አጥናፉ በበኩላቸው ትምህርቱን ከመስጠት ባለፈ በዘርፉ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያስተባብር የጥናትና ስልጠና ማዕከል ማቋቋማቸውን ገልጸዋል።
"በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው ማዕከል በዘርፉ ጥናትና ምርምር በማድረግ ፖሊሲ አውጪ ለሆኑ አካላት አስፈላጊውን ግብዓት ለማቅረብ ያግዛል" ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የፌዴራልና የክልል የዘርፉ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።