ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የነዳጅ ግብይት ክፍያን በዲጂታል ስርዓት መፈጸም የሚያስችሉ ሁለት መተግበሪያዎችን ስራ አስጀመረ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 16/ 2015 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የነዳጅ ግብይት ክፍያን በዲጂታል ስርዓት መፈጸም የሚያስችሉ ሁለት መተግበሪያዎችን ስራ አስጀመረ፡፡

የመተግበሪያዎቹን ስራ ላይ መዋል በተመለከተ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር እንዲሁም ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የመተግበሪያዎቹ ስራ ላይ መዋል በአገር አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ክፍያ ስርዓትን ለማዘመን ሚናው የጎላ ነው፡፡

አንደኛው መተግበሪያ ከዚህ በፊት ለተለያዩ ክፍያዎች አገልግሎት ላይ የዋለው "ሲቢኢ ብር" ሲሆን፤  ከዛሬ ጀምሮ ከዚህ በፊት ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ የነዳጅ ክፍያ ስርዓትን ለመፈጸም በሚያስችል መልኩ መቅረቡን አመላክተዋል፡፡

ሌላኛው "ፊውል አፕ" የተሰኘው አዲስ መተግበሪያ ደግሞ ለዚሁ አገልግሎት በባንኩ የቀረበ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ፤  በአዲስ አበባ ከዛሬ ጀምሮ መተግበሪያዎችን  ጥቅም ላይ ማዋል አንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

"አገልግሎቶቹ ጊዜን ቆጣቢ ከመሆናቸው ባላይ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር እንደሚያግዙ ጠቅሰዋል፡፡

ባንኩ ወደ ፊት መተግበሪያዎችን በስፋት በማቅረብ ህብረተሰቡ ወደ ባንክ መምጣት ሳይጠበቅበት ባለበት ቦታ ሆኖ የባንክ አገልግሎት እንዲያገኝ የጀመረውን ሰራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡


 

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በሪኦ ሐሰን በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ በትራንስፖርት ዘርፉ የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ባንኩ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበው በቀጣይም ተባብሮ መስራቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ከግንቦት አንድ ጀምሮ ስራ ይጀምራል ያሉት ሚኒስቴር ዴዔታው ለተግባራዊነቱም ቅንጅታዊ ስራ ስለሚጠይቅ በትኩረት ይሰራበታል ብለዋል፡፡


 

መተግበሪያዎቹ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የነዳጅ ሽያጭ ስርዓትን በማሳለጥ ለአገር ኢኮኖሚ እድገትን እንደሚደግፍ የተናገሩት ደግሞ የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ዜጎችን ቁጥር ወደ 18 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም