ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን  በአራት የአፍሪካ አገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት በታንዛኒያ ጀመሩ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 16/2015(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ  ጉዳይ  ሚኒስትር  ደመቀ መኮንን በአራት የአፍሪካ አገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት በታንዛኒያ  ጀመሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በታንዛኒያ፣  ኮሞሮስ ፣ ቡሩንዲና  ዩጋንዳ የሚያደርጉትን ጉብኝት  በታንዛኒያ ሲጀምሩ የታንዛኒያ አቻቸው ሲቴጎሚና ታክስ አቀባበል አድርገውላቸዋል። 


 

 አቶ ደመቀ ከታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሳሉሁ ጋር የህንድ ውቅያኖስ ከተማ በሆነችው በዛንዚባር  በሁለትዮሽና አከባብያዊ ጉዳዮች  ዙሪያ ተነጋግረዋል።

ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር ላላት ግንኙነት ትኩረት እንደምትሰጥ  ገልጸው በተለይ የኢኮኖሚውን  መሰክ ለማጠናከር እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት  ሳሚያ አገራቸው ከኢትዮጵያ  ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለይም በአቭዬሽን፣ ቱሪዝም እና በባህል ዘርፍ እንዲጠናከር ፍላጎቷ መሆኑን  አስረድተዋል።

መንግስት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በመተግበር ሰላምን ማፅናት እንደሚፈልግም  አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በውይይት እልባት እንዲያገኝ በመጠየቅ  የአረብ ሊግ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

በሱዳን ያለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ና የውጭ ጉዳይ  ሚኒስትር ደመቀ  ተናግረዋል።

የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት  አገራቸው የኢትዮጵያ መንግሥት  ሰላም ለማስፈንና ለማፅናት የሚያደርገውን ጥረት ትደግፋለች ብለዋል።

የህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመከላከል መግባባት ላይ መደረሱንና ታንዛኒያ ውስጥ  በአዘዋዋሪዎች ተታለው በቁጥጥር ስር የሚገኙ ዜጎቻችን ተገቢው አያያዝ እንዲደረግለቸው አቶ ደመቀ ጠይቀዋል።

በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ 2500 ዜጎቻችንን ባለፉት ወራት የመለሰ ሲሆን ቀሪዎቹንም ለአገራቸው እንደሚበቁ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም