የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ
አዳማ፤ ሚያዝያ 16/2015(ኢዜአ):- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኢንዱስትሪ የሰው ሃይል ፍላጎትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን መሰረት አድርገው እንዲሰሩ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ገለፁ።
የተቋማቱንና የኢንዱስትሪ ትስስር ለማጠናከር የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ለማዳበር የተዘጋጀ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ለኢዜአ እንደገለጹት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰው ሃይል ልማት ፕሮግራም ከወቅቱ የኢንዱስትሪና የገበያ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ መሆን አለበት።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር ረቂቅ አዋጁም ብቁና በተግባርና ክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል ለማፍራት ወሳኝ ሚና ያለው ነው ብለዋል።
በተለይም በመሃከላቸው በአሰራርና በሕግ ማዕቀፎች መሰረት የሚኖረው ትስስር ሀገሪቷ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በዕውቀት ልማት የምትፈልገው የሰው ሃይል እንዲገነባ ቁልፍ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የሰለጠነውን የሰው ሃይል የስራ አጥነት ቁጥር በመቀነስ ረገድ የሚኖረው አስታዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ የትምህርት ፕሮግራሞቹም የሀገሪቷን ልማትና ዕድገት በማገዝ በኩል ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው አዋጁ የዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማትና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች ከኢንዱስትሪ ጋር የሚኖራቸውን ትስስር የሚወስን ነው ብለዋል።
በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በክህሎት፣ በዕውቀትና ቴክኖሎጂ የዳበረ ብቁ የሰው ሃይል እንዲያፈሩ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
አክለውም የትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሞች እንዲሁም የምርምር ስራዎች የኢኮኖሚ ልማት ውጤታማነትን እንዲደግፉ የሚያስችላቸውን የህግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው ያስችላልም ብለዋል ።
የኢንዱስትሪ ሴክተርና ተቋማቱ የተቀናጀና ግልጽ የሆነ የትስስር ስርዓት እንዲኖራቸው ለማስቻልም ይረዳል ነው ያሉት።
የኢንዱስትሪ ዩኒቨርስቲ ትስስር ስትራቴጂ በመርህ ደረጃ ቢኖርም በህግና አሰራር ያልተደገፈ በመሆኑ ያመጣው ውጤት አናሳ መሆኑን ገልጸው፤ አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ተቋማቱና የኢንዱስትሪው ሴክተር በህግ የተደገፈ ግንኙነትና ትስስር እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል።
መድረኩ ረቂቅ ሰነዱን በግብዓት ለማዳበር የተዘጋጀ መሆኑንም አመልክተዋል።